ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለረጅም ዘመናት የቆየ ወዳጅነትና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር አላቸው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ለረጅም ዘመናት የቆየ ወዳጅነትና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር ያላቸው አገራት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ተኛ መደበኛ ስብስባ ዛሬ አካሄዷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ጉዳዮች አንዱ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ አንዱ ነው። 

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገና ከአገራት ጋር ግንኙነት የምትመሰርተውም መሰረታዊ ፍላጎቶቿን ለማስከበር ነው ብለዋል። 


 

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ትብብርን አስቀድማ እየሰራች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ የሰጠው ለጎረቤት አገራት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤቶቻችን ጋር በጋራ መልማት እንሻለን ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ የሶማሊያን ጉዳይ ማሳያ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱ አገራት ለረጅም ዘመናት የቆየ ወዳጅነትና ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትብብር እንዳላቸው አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሕልውና  የሚጎዳ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት ነው የተናገሩት።

የሶማሊያን ሰላም ለማስከበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውንና ይህ ዋጋ እየተከፈለ ያለው የሶማሊያ ሰላም የእኛ ሰላም ነው የሶማሊያ ልማት የእኛ ልማት ነው ብለን ስለምናምን ነው ብለዋል።  

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም