ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁንም ለመደራደር ዝግጁ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁንም ለመደራደር ዝግጁ ናት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አሁንም ለመደራደር ዝግጁ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁንም ለመደራደር ዝግጁ ናት ብለዋል።
ቀደም ብሎ የሕዳሴ ግድብ የግብጹን አስዋን ግድብ ውሃ መጠን ይቀንሳል የሚል አሉባልታ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላ ግን አስዋን ግድብ አልቀነሰም ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤቶች ንጹህ ውሃ ትሰጣለች" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያም ጥያቄዎቿን እንዲቀበሉ ትሻለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በሰጥቶ መቀበል መርህ በመመራት ተጋግዞ እና ተከባብሮ መኖር ትፈልጋለች ሲሉም አክለዋል።