የዋጋ ንረት ላይ የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ንረት ላይ የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016 (ኢዜአ)፦ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ሂደት የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዋጋ ግሽበትን በሚመለከት ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የዋጋ ንረት ትልቁ የሀገሪቱ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው በሌላው አለምም ከፍተኛ ችግር መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ኢትዮጵያ ለመቋቋም እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
ለዋጋ ንረት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚፈለገውን ያህል ምርት ያለማምረት፣ የጸጥታ ችግርና የገበያ ሰንሰለት አለመጠናከር፣ ጠንካራ የሪፎርም ስራዎች አለመስራትና ሌሎችንም ዘርዝረዋል።
በዚህም ምክንያት የዋጋ ንረትቱን በሚፈለገው ደረጃ ማረጋጋት አልተቻለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ የዋጋ ንረቱን ቀደም ሲል ከነበረበት 35 በመቶ አሁን ላይ ወደ 28 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ለዚህ መጠነኛ ለውጥ የስንዴ፣ የሩዝና ሌሎችም የግብርና ምርቶችን በብዛትና በስፋት ማምረት በመቻሉና በሌማት ትሩፋትም ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ምርትና ምርታማነትን ማጠናከርና ዘላቂ ሪፎርም ስራዎችን መስራት፣ ደሃ ተኮር የሆኑ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ላይ ትኩረት ተስጥቶ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 በጀት ዓመት የ7 ነጥብ 9 በመቶ እድገት የሚያስመዘግብ መሆኑንም ተናግረዋል።