ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍላለች- ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከ2011 ጀምሮ በአምስት አመታት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ በመክፈልና የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማቆም ትልቅ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር (ዶ/ር) ዐቢይ አሕመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ካስመዘገባቸው ትላልቅ ስኬቶች ዋነኛው እዳ ላይ የያዘው አቋም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስትበደረው የነበረው የንግድ ብድር አራጣ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ልማት ሳይሳካ ሀብታችንን መልሰን ለመስጠትና የእዳ ጫና ላይ የጣለ መሆኑን አስታስዋል።

የለውጡ መንግስትም ይህንን በመገንዘብ የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማቆም የነበረውን እዳ በመክፈል ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ2011 እስክ 2015 ዓ.ም ድረስ 9 ነብጥ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ መክፈል ተችሏል ብለዋል።

ከለውጡ በፊት የሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ የነበረው የውጭ እዳ በአሁኑ ወቅት ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው በቀጣይ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

የእዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሆና ላለፉት ሶስት አራት ዓመታት ስትጠይቅ መቆየቷን ጠቅሰው የፈጠነ መላሽ አለመሰጠቱን ተናግረዋል።

ሆኖም እጃችንን መጠምዘዝ የሚፈልጉ አካላት ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ ክፍያ መክፈል አልቻለችም የሚል መረጃ እያናፈሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እንኳን 33 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል አቅም ልታጣ ቀርቶ በአምስት ወራት ብቻ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ የገቢ ምርት ከውጭ ያስገባች ሀገር ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለት ቀን ገቢው ለሆነው  33 ሚሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ይህንን ለመክፈል የምትታማ ሀገር እንዳልሆነች ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አቅሙ እያላት መክፈል ያልቻለችው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም የእዳ ቅነሳና ሽግሽግ ላይ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች እኩል ምላሽ እስኪያገኙ ለአንድ ወገን ቀድሞ ላለመክፈል ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም