ቀጥታ፡

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከተሰጠው 170 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ ነው

 አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016 (ኢዜአ) በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከተሰጠው 170 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ሲሆን ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ  (ዶ/ር)  ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የኢኮኖሚና የፋይንናስ ጉዳይ ሲሆን መንግስት ለዓመታት የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በማክሮ ፋይናንስ ስራዎች ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ጠቅሰው በፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎች እና ስራዎች ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ መንግስት የሚተርፉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ ረገድ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 100 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መጨመሩን ገልጸዋል።

ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1 ነጥብ 2 ትርሊዮን ብር በላይ መድረሱን አንስተዋል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 170 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀድሞ ጊዜ 70 ከመቶው ለመንግስት ሲሰጥ ከነበረው ብድር አንፃር ለግሉ ዘርፍ ትልቅ እምርታ ነው ብለዋል።

በሞኒተሪ እና በፊሲካል ፖለሲ የተወሰዱ እርምጃዎች  ከባድ ጫና ውስጥ የነበሩትን የኢትዮጵያ ንግድና ልማት ባንኮችን መታደግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚ ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ደረጃም በግብርና ዘርፍ ባለፈው ዓመትም ሆነ ዘንድሮ ከፍተኛ ዕምርታ መምጣቱን ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም ጠቁመዋል።

በትራንስፖርት ፣በማዳበሪያ አቅርቦት፣ በአይሲቲ እና ሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በአጠቃላይ ዘንድሮ 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ገልጸው ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም