ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካፒታል ገበያ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካፒታል ገበያ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀመር ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካፒታል ገበያ የዝግጅት ጊዜውን አጠናቆ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብስባውን እያደረገ ይገኛል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢኮኖሚውን ዘርፍ አስመልክቶ እየሰጡት ባለው ማብራሪያ ካነሷቸው ኃሳቦች መካከል የካፒታል ገበያ ይጠቀሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካፒታል ገበያ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን ይህ የፋይናንስ ግብይት ሥርዓት ሲጀመር በርካታ ኢ-መደበኛና ሕገ-ወጥ ኃብት ወደ ትክክለኛ ሕጋዊ መሥመር ገብቶ በርካታ ኢንቨስትመንት ለመፍጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ሥራውን ለማስጀመር ተቋም ተመስርቶ የሕግ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙና የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፈንድና ኃብቶች እንደሚያስተዳድርም ጠቁመዋል።
የካፒታል ገበያው ወደ ሥራ ሲገባ አሰራሮችን ሕጋዊ በማድረግ ብዙ ለውጦችን ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት እንዲያጠናክር የካፒታል ገበያ 'በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013' ተቋቁሟል።
በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ "የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን" መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነድ መዋዕለ ነዋዮችን በማውጣት የግብይት ሥርዓቱን ፍትኃዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር የመፍጠር ሥልጣን ተሰጥቶታል።
ኢንቨስተሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያውን ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።