ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ተያዘ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016 (ኢዜአ)፦ ለሽብር ወንጀል ሊውል የነበረ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ከእነተጠርጣሪው መያዙን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪው ከሸኔ የሽብር ቡድን የጥፋት ተልዕኮ በመቀበል ሽብር ለመፈፀም መነሻውን ከአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ በማድረግ በግለሰብ እጅ የማይያዙ ሕገ-ወጥ የቡድን የጦር መሣሪያዎች (አንድ RBG Launcher እና አንድ ብሬን አምስት አጭር ርቀት መገናኛ ሬድዮ እና አራት ቻርጆችን ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ-3 ኢት 10492 በሆነ ፒክ-አፕ (pickup) መኪና ጭኖ ወደ ኦሮሚያ ክልል ኤጀሬ አካባቢ ለሽብር ቡድኑ ሊያደርስ ሲንቀሳቀስ ልዩ ቦታ አሸዋ ሜዳ በተባለ አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተጠቅሷል።
ፖሊስ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር የጦር መሣሪያዎችን ከነ-ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራበት እንደሚገኝ ተገልጿል።
እነዚህ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች በሽብር ቡድኑ እጅ ቢገቡ ኖሮ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ ይችሉ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።
ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ለመቆጣጠር በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ከምን ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፖሊስ ገልጿል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር ተገቢውን ቅንጅት በማድረግ በየትኛውም ደረጃ የሚወጠኑ የሽብር ተግባራትን ለመቆጣጠር የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል።