ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትና በጋራ የመልማት እቅድ የቀጣናው አገራት ሊደግፉት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትና በጋራ የመልማት እቅድ የቀጣናው አገራት ሊደግፉት እንደሚገባ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የፈረሙት የትብብርና የአጋርነት መግባቢያ ሰነድ በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች የወደብ አጠቃቀምን ጨምሮ ለሚኖራቸው ግንኙነት ማዕቀፍ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል፡፡

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን  አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ  ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት የሰጥቶ መቀበል መርህ በተግባር የተገለጠበት ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ጋር ያደረጉት ስምምነት ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ከቀጣናው ሀገራት ጋር  በትብብርና አብሮነት ለማደግ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢኮኖሚ እድገትና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ባሻገር ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ንግድን ለማሳለጥ የጎላ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት።

ከዚህም ባሻገር በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና  ያለውን የፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና  የፀጥታ ሁኔታ በአዎንታዊ መልኩ ይቀይረዋል ነው ያሉት፡፡ 

በመሆኑም የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎትና በጋራ የመልማት እቅድ የቀጣናው አገራት በቅንነት በመመልከት ሊደግፉት ይገባል ብለዋል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደብን በትብብር ከመጠቀም ጋር በተያያዘ ታንዛኒያን በአብነት ያነሱት አምባሳደር ሽብሩ፤ ከሚያዋስኗት ስምንት ሀገራት ጋር ባሏት ሰባት ወደቦች በጋራ ትሰራለች ብለዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል በትብብር የተሰሩት የባቡርና ሌሎች የየብስ ትራንስፖርት እንዲሁም የወደብ መሠረተ- ልማት አውታሮች አስደናቂ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የታንዛኒያ መንግሥት ለዛምቢያ 20 ሄክታር ገደማ ወደብ ከማበርከቱም ባለፈ የዛምቢያ ሸቀጥ ለ45 ቀናት ያለምንም ቀረጥ ወደቧ ላይ እንዲቆይ ፈቅዳለች ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር ተጠቃሚነት ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ጭምር መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም