የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እድገት ጥሩ መሠረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እድገት ጥሩ መሠረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ለሀገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እድገት ጥሩ መሠረት የሚጥል መሆኑን የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ገለጹ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የፌዴራል ተቋማት የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ኢዜአ ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በዛሬው እለት ጎብኝተዋል።
የዘመኑን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን እንዲሁም ጅምናዚየምና ሌሎችንም አገልግሎቶች ያሉት የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ባለፈው ሳምንት ተመርቆ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ከተመረቀ በኋላ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እየጎበኙት ሲሆን በዛሬው እለትም የኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች ጎብኝተውታል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፤ ኢዜአ ሀገራዊ መግባባት የመፍጠር ኃላፊነቱን ከመወጣት ባለፈ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያግዙ የይዘት ሥራዎችን ለዓለም ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት መልክ ያላቸው ዓለም አቀፉንና የጎረቤት ሀገራትን ታሳቢ ያደረጉ፤ የሀገሪቱን አቋም እና ፍላጎት የሚያንፀባርቁ የይዘት ሥራዎችን ይዞ መቅረብ እንዳለበትም ገልፀዋል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የደረሱበትን አቅም ያሟላ በመሆኑ ከተቋሙ አልፎ ለሀገሪቷ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን እድገት ጥሩ መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራል ተቋማት ክትትልና ድጋፍ ዴስክ ኃላፊ አብርሃም በዕውቀት፤ ኢዜአ በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በአዲስ ይዘትና አቀራረብ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆኖ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፌዴራልና የክልል ተቋማት የክትትል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከበበ ዳዲ፤ የኢዜአ ሚዲያ ኮምፕሌክስ እጅግ ዘመናዊና ትልቅ የሀገር ኃብት በመሆኑ ሁላችንም ኮርተንበታል ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ሕዝቅኤል፤ ኢዜአ በሚዲያው ዘርፍ ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ተጠቃሽና ስመ-ገናና መሆኑን ገልፀዋል።
ለሚዲያዎች የተሟላና ትክክለኛ የዜና ግብዓት አቅራቢነቱም በኢትዮጵያ ብቸኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ከተመሠረተ 80 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት በትጋት እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።