የኢትዮ-ሩሲያ ቢዝነስ ፎረም በሞስኮ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ሩሲያ ቢዝነስ ፎረም በሞስኮ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሩሲያ ረዥም አመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያ ስላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያና የሩሲያ የቢዝነስ ፎረም በሞስኮ ከተማ ተካሒዷል።
ፎረሙ በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ በሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት፣ በCoordinating Committee for Economic Cooperation with African Countries (AFROCOM) እና በሩሲያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀ የተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል።
በፎረሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያ ስላሴ ኢትዮጵያና ሩሲያ ረዥም አመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ግንኙነት በኢኮኖሚው መስክም መደገም እንደሚኖርበት ያመለከቱት ኮሚሽነሯ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የሩሲያ የንግድና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፓዳልኮ እና የAFROCOM ሊቀመንበር ኢጎር ሞሮዞቭ ባስተላለፉት መልዕክት ሩሲያና ኢትዮጵያ ያላቸው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ጠንካራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ከአፍሪካ አገራት ጋር በኢኮኖሚው መስክ የተሻለ ትስስር ለመፍጠር እያደረገች ላለችው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ የንግድ ቢሮ በአዲስ አበባ ከፍታ እየሰራች መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም ይህ ጥረት የተሻለ ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ለመስራት ሩሲያ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
በፎረሙ ላይ አገራችን ትኩረት በሰጠቻቸው ዋና ዋና መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ ከ100 በላይ የሩሲያ እና 30 የአገራችን የንግድ ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።