የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕምና አመራረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚገባ ነው- የዘርፉ ተዋንያን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕምና አመራረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚገባ ነው- የዘርፉ ተዋንያን

ጥር ፤27/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕም፣ የአመራረት እና የአፈላል ሥርዓት ለዓለም ተሞክሮ እንደሚሆን ከተለያዩ ሀገራት የመጡ የዘርፉ ተዋንያን ገለጹ።
ዓለም አቀፍ የቡና ተዋንያን በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ በ450 ሄክታር ላይ የለማ የቃርጫንሼ ደበቃ ዘመናዊ የቡና እርሻ ልማትን ጎብኝተዋል።
ዘመናዊ አሰራሩ ከኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ቡና ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያላትን ተሳትፎ በእጅጉ የሚያልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ መካከል የፔሩ ዜግነት ያላቸው ቪክቶር ሶሊያና አገራቸው ፔሩ ለቡና ልማት የሚመች የተፈጥሮ ጸጋ ቢኖራትም በዘርፉ ያላት ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው።
የተሻለ አሰራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ልምድ ለመቅሰም ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ደረጃ በልዩ ጣዕሙ እንደሚታወቅና ተወዳጅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ቡና በኢትዮጵያ በጫካ፣ በጥላ ዛፍ እና በጠብታ መስኖ ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ከመልማቱ ባለፈ እራሱን የቻለ ባህላዊ አሰራር እንዳለው በመስክ ምልከታው መገንዘባቸውን አስረድተዋል።
ይህም ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን ነው የገለጹት።
"በቡና ልማት ዝቅተኛ ተሳትፎ ቢኖረንም ምርቱን እሴት ጨምሮ ለገበያ በማቅረብ በኩል ተሳትፏችን የላቀ ነው" ያሉት ደግሞ በቡና ንግድ ሥራ የተሰማራችው የባንግላዲሽ ዜግነት ያላት ሱሪያ አክትር ናት።
ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ እሷን ጨምሮ ወጣቱ ትውልድ ወደቡና ልማት በስፋት እየገባ መሆኑን ጠቁማ፣ በእዚህም በቡና ልማት የተሻለ ልምድና ባህል ወዳላት ኢትዮጵያ መምጣቷን ገልጻለች።
በኢትዮጵያ ከጥላ ዛፍና ከጫካ ቡና ልማት በተጓዷኝ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጠብታ መስኖ ልማት መመልከቷን የገለጸችው ሱሪያ፣ ይህም የተለየና በዘርፉ ፈጠራና አዲስ አስተሳብ እየታከለ መምጣቱን ያሳያል ብላለች።
በዓለም ላይ በስመጥር የንግድ ምልክቶች የሚሸጡ ቡናዎች ገበያውን ቢቆጣጠሩም የኢትዮጵያ ቡና የተለየ ጣዕም ያለው የምርት አያያዝና የቡና አፈላል ሥርአቱም ልዩ መሆኑን ገልጻለች።
በዩጋንዳ የቡና አምራች አርሶ አደሮች የዘላቂ ወዳጅነት ማዕከል ዳይሬክተር ሮናል ሂጂሮ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ እና የቡና ልማት ቁርኝታቸው ከንግድና ኢንቨስትመንት የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከፍተኛ ከመሆኑ ባለፈ ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ለማህበራዊ መስተጋብር መሰረት የጣለ መሆኑን አስረድተዋል።
በዩጋንዳ የቡና ልማት በተበጣጠሰ መሬት በባህላዊ ስርዓት እንደሚመረት ጠቁመው፣ ይህም ምርታማነትን ከመቀነስ ባለፈ በመሬት አጠቃቀም ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው ከዝናብ ጥገኝነት የተላቀቀ ዘመናዊ የቡና ልማት በአፍሪካ የተለየና ትልቅ ጅምር መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም ከኢትዮጵያ ልዩ ጣዕም ቡና ጋር ተዳምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ያላትን ተሳትፎ በእጅጉ የሚያልቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ልማት ያላትን አቅም እንድትጠቀምና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ቴክኖሎጂ መጠቀም ግዴታ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የቃርጫንሼ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እስራኤል ደገፉ ናቸው።
ድርጅቱ የደበቃን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከ3 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ዘመናዊ የቡና እርሻ ልማትን በሄክታር ከ46 ኩንታል በላይ ምርት እየሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም እንደ አገር ካለው አማካይ የቡና ምርታማነት አንጻር ከስድስት እጥፍ በላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቡናን በጠብታ መስኖ ቴክኖሎጅ ከጥላ ዛፍ ውጭ በማልማት ከአፍሪካ የመጀመሪያ መሆኑን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱም ከ25 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምዕራብ ጉጂ ዞን የአባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸናፊ ዘውዴ በበኩላቸው ዘመናዊ የቡና ኢንቨስትመንትን ወደ አካባቢያቸው መምጣት ከምርት ውጭ የሆነ ገላጣ መሬት ወደ ምርት እንዲገባ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ይህም የወረዳውን የቡና አቅርቦት ከማሳደግ ባለፈ በአቅራቢያ ላሉ አርሶ አደሮች የእውቀትና የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ዘርፉን በዘመናዊ ተክኖሎጂ ማበረታታት እንደሚገባ ያመላከተ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በመስክ ምልከታው የአፍሪካ ጥሩ ቡናዎች ማህበር፣ የአፍሪካ ቡና አምራቾችና የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ቡና አምራች አካባቢዎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።