በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናትና ልማትን ለማስቀጠል ትብብርን ማጠናከር ይገባል - ዶክተር አህመዲን መሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናትና ልማትን ለማስቀጠል ትብብርን ማጠናከር ይገባል - ዶክተር አህመዲን መሐመድ
ደብረ ብርሀን፤ ጥር 27 /2016(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል ሰላምን በዘላቂነት ለማፅናትና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን ለማስቀጠል ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር አህመዲን መሐመድ ገለጹ።
በሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተመለሱ ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቅለዋል።
በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።
የክልሉን ህዝብ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ መንግስት በተደራጀ አግባብ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ውጤታማነትም ሁሉም የድርሻውን በመወጣት መተባበር እንዳለበት አመልክተዋል።
በለሚ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉትም በአካባቢያቸው በሰላም ማስከበርና በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ህዝባቸውን መካስ ይገባቸዋል ብለዋል።
የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢና የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል አበባው ሰይድ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን የነዋሪዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ሰራዊቱ የህግ ማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡ ከሰራዊቱ ጎን ሆኖ እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
በህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ መንግስት አበክሮ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት አባልና የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ ናቸው።
በተሳሳተ መንገድ አፍራሽ ተግባር ለመፈጸም የሚደረግ ሙከራን በማምከን ወጣቱ ለሰላም መስፈንና ልማት መቀጠል ግንባር ቀደም ሆኖ መቆም እንዳለበትም አሳስበዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ የተቀላቀሉትን በማህበር በማደራጀት በገቢ ማስገኛ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ተገቢው እገዛና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማህበረሰቡ ከተቀላቀሉት መካከል ሀምሳ አለቃ ዘላለም ገብረህይወት በሰጡት አስተያየት፤ ይጓዙበት የነበረው መንገድ አጥፊና ጎጂ መሆኑን በመረዳት ወደ ሰላም መመለሳቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላም ገብተውበት የነበረው ችግር አስከፊነትን በማስተማር ለሰላም መስፈን አበክረው ለመስራት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በስነ ስርዓቱም በየደረጃው ያሉ የአመራር አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ሌሎችም የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።