ቀጥታ፡

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማትና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበት ቅንጅታዊ ስራ ይጠይቃል

ጋምቤላ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማትና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማጎልበት የጋራ ቅንጅታዊ ስራ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሰልጣን ገለፀ።

ባለስልጣኑ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለማልማት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ መንግስት ጋር መክሯል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ሰፊና እምቅ የብዝሃ ህይወት ያለበት አንጋፋ ብሔራዊ ፓርክ ነው።

ይሁን እንጂ ባለው አቅም ልክና በሚፈለገው ደረጃ ባለመልማቱ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ጥቅም ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት ፓርኩን በአግባቡ አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ከሌሎች የአፍሪካ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር በዘላቂነት ለማልማት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።

በመሆኑም ፓርኩን አልምቶ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት የክልሉ መንግስት ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።


የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙት የብዝሃ ልማቶች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሚውል ሀብት ቢኖረውም በአግባቡ ባለመልማቱ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ የሚፈለገውን ጥቅም ሳያስገኝ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም ፓርኩን ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ 4 ሺህ 750 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በውስጡ 69 የአጥቢ፣ 327 የአዕዋፍ፣ 7 የተሳቢ እንስሳትና 493 የዕፅዋት ዝርያዎች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም