በየዓመቱ የሚካሄደውን የፈረስ ጉግስና ባህላዊ ትርኢት ትልቅ የቱሪዝም ሃብትና እሴት ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ):-በየዓመቱ የሚካሄደውን የፈረስ ጉግስና ባህላዊ ትርኢት ትልቅ የቱሪዝም ሃብትና እሴት ማድረግ እንደሚገባ የጨፌ ኦሮሚያ  ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ኤልያስ ኡመታ ገለጹ።

ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የተሳተፉበት ዓመታዊ የፈረስ ግልቢያ ውድድርና ባህላዊ ትርኢት በሰንዳፋ በኬ ተካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የጨፌ ኦሮሚያ  ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ኤልያስ ኡመታ፤ የፈረስ ጉግስና ትርኢት ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ትልቅ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥንት ጀምሮ የጀግንነት ምልክትና ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ጉልህ አስተዋፅኦ እንደነበረው አንስተዋል።

በመሆኑም በየዓመቱ የሚካሄደውን የፈረስ ጉግስና ባህላዊ ትርኢት ትልቅ የቱሪዝም ሃብትና እሴት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የባህላዊ የፈረስ ውድድርን የቱሪዝም ሃብት ማድረግና እሴቱን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ ለማስተላለፍ በክልሉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዝናሽ አበቤ፤ በበኩላቸው በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው ብለዋል።

በመሆኑም የፈረስ ውድድሩ ካለው ባህላዊ እሴት፣ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር በቀጣይ የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም