ቀጥታ፡

የባሕር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ ፕሮጀክት አስፓልት ንጣፍ ስራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥር 27/2016(ኢዜአ)፦ በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ግዙፉ የአባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አስፓልት ንጣፍ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ።

ከሄኒ ጋርደን አደባባይ እስከ ዘንዘልማ መገንጠያ ድረስ የሚዘልቀው 4 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባሕር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ መዳረሻ መንገድ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት እንዲሁም የመፋሰሻ ቱቦ ዋና ዋና ስራዎች በአብዛኛው መጠናቀቁም ተመላክቷል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ያለበት የአፈፃፀም ደረጃ 38 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአስፋልት እና የትራፊክ ምልክቶችና የመንገድ ላይ መብራቶች ተከላ፣ የቀለም ቅብ ስራዎችእንዲሁም የእግረኛ መንገድ ንጣፍ በስፋት ለመጀመር ከፍተኛ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

የመንገዱን ግንባታ ለማከናወን የተመደበውን 825 ሚሊዮን 659 ሺህ 857 ብር ሙሉ ለሙሉ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑም በመረጃው ተገልጿል።

መንገዱ የእግረኛ እና አካፋይን ጨምሮ መደበኛ ቦታዎች ላይ 51 ሜትር እንዲሁም የህዝብ ማጓጓዣ ማቆሚያ ቦታዎች ላይ 59 ሜትር ስፋት አለው፡፡

በተጨማሪም በአንድ ጊዜ በግራ እና በቀኝ 6 መኪናዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን የመኪና ማቆሚያ ቦታንም አካቶ የሚገነባ ፕሮጀክት ነው፡፡

መንገዱ የኢትዮ ሱዳን ዋና መስመር የሆነው የአዲስ አበባ - ባሕር ዳር - ጎንደር - መተማ መንገድ አንዱ ክፍል መሆኑም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት ሲሆን በአገልግሎት ብዛት የተጎዳውን ነባር የባሕር ዳር አባይ ወንዝ ድልድይ የትራፊክ ጫና እንደሚያስተነፍስ አስተዳደሩ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም