ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መግባቢያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ አለው - ምሁራን

ድሬዳዋ ፤ጥር 26/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን የሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ይህን የተናገሩት የሰላም ሚኒስቴር በድሬዳዋ "ሰላም ግንባታ፡ ቀጣናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጀውና በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎችና የሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በተሳተፉበት መርሃ ግብር ላይ ነው።

የሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር አብዱላሂ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በሰጥቶ መቀበል መርህ በመጓዝ የጋራ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው።

በሶማሌላንድና በኢትዮጵያ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በሰጥቶ መቀበል መርህ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ፈርቀዳጅ ተግባር መሆኑን በማከል።

እንደ መምህር አብዱላሂ ገለፃ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎችን ለማገዝ በድሬዳዋ የተካሄደው ውይይት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።


 

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሐመድ በበኩላቸው፤ ሀገራችን በሰጥቶ መቀበል መርህ የአመታት ጥያቄዋን ለመመለስ እያከናወነችው ያለው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።

የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ የምሁራን ሚና ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በማከል።

ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ እንዲሳካ ምሁራንን በቅርበት በማሳተፍ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ይህም የትውልድን ፋላጎትና ህልውና ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።


 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተማም አወል የመግባቢያ ስምምነቱ የቀጣናውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ተማም፤ ሌሎቹ የቀንዱ ሀገራት ወደ ስምምነት ማዕቀፉ በመግባት የተሻለ ብልፅግና፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ መትጋት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም