ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የተሳተፉበት የፈረስ ጉግስ ውድድር በሰንዳፋ በኬ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ጥር 26/2016(ኢዜአ)፦ ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች የተሳተፉበት ዓመታዊ የፈረስ ጉግስ ውድድርና ትርኢት በሰንዳፋ በኬ ተካሄደ።

ከውድድሩ ባለፈ የባህል ምግቦችና አልባሳት፣ የባህላዊ ቁሳቁሶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የባህል ቡድኖችም ተገኝተዋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ ደራራ ከተማ፤ በኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ ክዋኔ ውስጥ ፈረስ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት በሰንዳፋ በኬ በተካሄደው የፈረስ ጉግስ ውድድርና ትርኢት ከ4 ሺህ በላይ ፈረሰኞች መሳተፋቸውን ጠቅሰው ሁነቱ ጥልቅ እሴቶች የተንጸባረቁበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከውድድሩ በተጓዳኝ የባህል ምግቦች፣ አልባሳት፣ የባህላዊ ቁሳቁሶችና ሌሎችም ሃብቶች ለእይታ የቀረቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በኦሮሚያ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት በርካቶችን ባሳተፈና ባማረ መልኩ በየአመቱ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

የሰንዳፋ በኬ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ዝናሽ አበቤ፤ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የፈረስ ግልቢያና ትርኢት ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ባህላዊ ኹነትና የአስተዳደር ሥርዓት አብሮ የኖረ እና ታሪካዊ ትስስርም ጭምር እንዳለው አንስተዋል።


 

በመሆኑም የፈረስ ውድድሩ ካለው ባህላዊ እሴት፣ የገጽታ ግንባታና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር በቀጣይ የተጠናከረ ስራ ይሰራል ብለዋል።

በዛሬው እለት በውድድሩ ለተሳተፉ ፈረሰኞች የምስክር ወረቀት እንዲሁም ለአሸናፊዎች የዋንጫና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም