ቀጥታ፡

በሁኔታዎች የማይበገር የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016(ኢዜአ)፦በሁኔታዎች የማይበገር የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ገለጹ።

የቻይና አዲስ ዓመት ክብረ በዓል ማምሻውን በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።


 

አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛ ምሥራቅ፣ የኤዥያና በፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋን ጨምሮ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማቶች እና በኢትዮጵያ የቻይና ማህበረሰብ አባላት በዓሉን ታድመዋል።

 የቻይና ባሕላዊ ትዕይንተ ጥበባትን ጨምሮ የሀገሪቷን ባሕላዊና ኪና ጥበባዊ መልኮች የሚያስቃኙ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በዚህ ወቅት እንዳሉት የቻይናን አዲስ ዓመት ስናከብር ከኢትዮጵያ ጋር በአዲስ መንፈስ ለመስራት የምናረጋግጥበት ነው ብለዋል።

ቻይና በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገትን ማስቀጠሏን ጠቁመው፣ ሰላማዊ ልማትና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን እንደምትከተልም ገልፀዋል።

የተጠናቀቀው የፈረንጆች 2023 ዓመት ለኢትዮጵያና ቻይና ግንኙነት መጎልበት ልዩ ዓመት ነበር ያሉት አምባሳደሩ፣ 'የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ'ን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የልማትና የሰላም ትብብሮች በተግባር የታዩበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

ከነባሩ ጥብቅ አጋርነታቸው ባሻገር የኢትዮጵያ የብሪክስን ጎራ መቀላቀል ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በኮሙኒኬሽን፣ በፋይናንስ፣ በባህል፣ በትምህርትና በሌሎች መስኮች የነበሩ ትብብሮች ይበልጥ እንዲጎለብቱ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ይህም ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት እና ትስስር መጠናከር ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ነው ያነሱት።

በቀጣይም ቻይና በምንም ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ  ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማጎልበት እና 'የቤልትና ኤንድ ኢኒሼቲቭ'ን ግንባታን በማጠናከር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

በሁኔታዎች መለዋወጥ የማይለወጠውን የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እጅ ለዕጅ ተያይዘን እንሰራለን ብለዋል።

የጨረቃ አቆጣጠር ስሌት የሚከተለውን እና የክብረ በዓል ትዕምርቱን 'ድራጎን' ያደረገው የቻይና ዓዲስ ዓመት መከበር ከጀመረ ከ3 ሺህ ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ይነገራል።

የቻይና አዲስ ዓመት ዘንድሮ በፈረንጆቹ ከየካቲት 10 እስከ 15 ቀን 2024 በይፋ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም