ቀጥታ፡

የቀጣናው አገራት ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ሰላምን ለማጽናት በጋራ ሊቆሙ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ቀንድ አገራት ስትራቴጂካዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ሰላምን ለማጽናት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ ተገለጸ።

የሰላም ሚኒስቴር በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እንዲሁም ከሀርጌሳና ጅቡቲ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ቀጣናዊ የሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ ልማትና አካባቢያዊ አብሮነት ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል።  

የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም የመድረኩን ዓላማ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥ የአፍሪካ ቀንድ በርካታ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እያስተናገደ የመሆኑን ያህል አገራት በትብብር እድገታቸውን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲያግዙ ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጣናው አገራት በህዝብ ለህዝብ፣ በመንግሥት ለመንግሥትና በኢኮኖሚ መልካም ትብብር እንዳላቸው ገልጸው ይህንን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በምርምርና ማኅብረሰቡን በማስተባበር ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኘነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ በፍጥነት እያደገ የሚገኝ የሕዝብ ቁጥርና የውጭ ጫና እንዳለባቸው አውስተዋል።


 

ቀጣናው እምቅ የመልማት አቅም ቢኖረውም ትብብርን ማጠናከርና ሰላምን ማፅናት ካልተቻለ የሚፈለገው ብልፅግና አይረጋገጥም ብለዋል።

በመሆኑም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የቀጣናውን አብሮነት ለማጠናከርና የጋራ እጣ ፈንታን ለማሻሻል የሚደረገውን ጉዞ ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል።

በመድረኩም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የፀጥታና ደኅንነት ሥጋቶች፣ የሰላም ግንባታና የልማት ትብብር ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሑፎች ቀርበዋል።

ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት በዲፕሎማትነት ያገለገሉት አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ፥ ባቀረቡት ፅሑፍ፥ የአፍሪካ ቀንድ የሚታወቅባቸው መገለጫዎች ያሉት ሲሆን ብዝኃ መልክዓ ምድር ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ፣ ብዝኃ ባህልና ታሪክ ያለው ነው ብለዋል።


 

በቀጣናው ካሉ ዋና ዋና የፀጥታ ችግሮች መካከል ሽብርተኝነት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የድንበር ውዝግብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የሚያስከትላቸው የኃብት ሽሚያና ግጭት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ብልፅግናን እውን ለማድረግ ወታደሮቿን በጎረቤት አገራት ሱዳንና ሶማሊያ ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በማስማራት ፋናወጊ አስተዋጽዖ ማድረጓን ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነት በጋራ የመልማት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የብዝኃ ማኅበረሰብ የጋራ ኃብት መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ፥ በቀጣናዊ የልማት ትልሞቿ የጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተጋች ነው ብለዋል።

በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የባህልና ማኅበራዊ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ጄይላን ወልይ፥ ድንበር ተሻጋሪ ትብብር፣ ቀጣናዊ ትስስርና የሰላም ግንባታ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ፅሑፍ፥ ኢትዮጵያ ጅቡቲና ሶማሌላንድ በመልክምድርና በህዝብ የተሳሰሩ ናቸው ብለዋል።


 

ዓለም በአሁኑ ወቅት አዲስ አካባቢያዊ ትስስርና የትብብር ብሎኮችን እያስተናገደች ሲሆን፥ የኃይል አሰላለፉም ከአንድ ወገን ወደ ባለብዙ ወገን እየተቀየረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ቀንድ መልካም እድሎችና ሥጋቶች እንዳሉበት ተናግረው፥ ሽብርተኝነትን፣ የድንበር ግጭትንና ሌሎች ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ አንስተዋል።

ለዚህም የጋራ ልማትን በማፋጠን፣ የህዝብ ለህዝብና የባህል ትስስርን መሰረት ያደረገ የሰላም ግንባታን በማጠናከር ጠንካራና ጫናዎችን የሚቋቋም ቀጣና ሊፈጥሩ እንደሚገባ አንስተዋል። 

በሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የግጭት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር ናስር መሀመድ፥ ሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ በቀጣናው ልማትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማፅናት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ ዜጎች ነጻ የትምህርት እድል በመስጠትና ብቁ የሰው ኃይል ግንባታን በማገዝ ባለውለታ አገር መሆኗንም ተናግረዋል።

የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶ፥ ባህላዊ የገጭት መፍቻ ዘዴዎች ለሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና ላይ ያተኮረ ፅሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፥ በቀጣናው የሰላም ግንባታ ሂደት ቢኖርም ተጨባጭ ውጤት አለማምጣቱን ገልጸዋል።


 

በቀጣይ አካታች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ የእርቅና ምክክር እሳቤን በማስረፅ፣ የሲቪል ማህበራትና የግሉን ዘርፍ ያሳተፉ የሰላም ግንባታ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ገልጸዋል።

ማኅበረሰብ አቀፍ የሰላም ግንባታ ኢኒሼቲቭን  ማጠናከርም ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም