የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰመራ ለሚያስገነባው የወንጀል ምርመራ ቢሮ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰመራ ለሚያስገነባው የወንጀል ምርመራ ቢሮ መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ለሚያስገነባው የወንጀል ምርመራ ቢሮና የመኖሪያ ቤት ፕሮጀክት መሠረተ ድንጋይ ተቀመጠ።
የመሰረተ ድንጋዩን ያስቀመጡት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ ናቸው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት የፌደራል ፖሊስ እያካሄደ ባለው የሪፎርም ስራ መሰረት በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ዛሬም የወንጀል ምርመራ ማዕከልን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ለመገንባት 10ሺህ ካሬ ሜትር መሬት በመረከብ የመሠረተ ድንጋይ መጣሉን ተናግረዋል።
ከማዕከሉ በተጨማሪም በክልሉ ለሚሰሩ የፖሊስ አመራሮችና አባላት የመኖሪያ ቤት እንዲመቻች እና ለወንጀል መከላከልና ምርመራ የሚያግዙ ዘመናዊ የስልጠና ማዕከላትን ያካተተ ግንባታ እንደሚከናወንም ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ተቋሙ በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚቃጡ ከፍተኛ ወንጀሎችን በመከላከልና መርምሮ ለህግ የማቅረብ፣ ከተለያዩ ፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የታቀዱ ትላልቅ ወንጀሎች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የመቆጣጠር ስራዎችን ስኬታማ በሆነ መልኩ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በወንጀል መከላከሉም ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ በርካታ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ አስታውቀዋል።
የሰመራ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የክልሉም ሆነ የከተማውን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ የሚያፋጥን ከመሆኑም ባሻገር ለአካባቢው ማኅበረሰብ የስራ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
ከንቲባው አያይዘውም ፕሮጀክቱ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።