ቀጥታ፡

ሰራዊቱ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ብቃትና ዝግጁነት አለው -ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ኦሮሚያ፤ ጥር 25/ 2016 (ኢዜአ) የመከላከያ ሰራዊቱን የአመራር ሚናን ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት አገሩንና ህዝቡን የሚወድ ሰራዊት የመገንባት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በ24ኛው ዙር የአንድነት ኮርስ ሰልጣኝ እጬ መኮንኖችን አስመርቋል። 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰራዊቱ ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ ብቃትና ዝግጅት አለው ብለዋል።

 "ከመቼውም ጊዜ በላይ እራሳችንን አጠናከረን ከየትኛውም በኩል የሚሰነዘር ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነን" ነው ያሉት። 

ለዚህም የሰራዊቱን አቅምና የአመራር ሚናን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ህዝቡን የሚወድና አገሩን የሚያስቀድም ሰራዊት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ይቀጥላልም ብለዋል። 

የዛሬ ተመራቂዎችም አገርን መጠበቅ የሚያስችል አቅም መገንባታቸውን ገልፀው የሚጠበቃቸውን ግዳጅ በብቃት ለመወጣትም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

"በስልጠናው ያገኛችሁትን እውቀትና አቅም በተግባር በማዋል አቅማችሁን ማጎልበት አለባችሁ" ሲሉም አስገንዝበዋል።

በመከላከያ ትምህርት እና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል ይመር መኮንን የሰራዊቱ የአቅም ግንባታ ስልጠና በተከታታይ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። 

ተቋሙ ግልጽ የስልጠና አቅጣጫ አስቀምጦ በጽኑ ወታደራዊ ዲሲፕሊን ብቃት ያላቸው አባላትን የማፍራት ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል። 

በዚሁ መሰረት ምቹ የስልጠና ተቋማትን የማዘጋጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተመስገን አቦሴ በበኩላቸው ተመራቂዎች ከአካዳሚው ያገኙትን እውቀት አገራቸውን እንዲያገለግሉበት አሳስበዋል። 

ተመራቂዎቹ በስልጠናው የተሻለ የግዳጅ አፈጻጸም እንዲኖራቸው የሚያግዙ ኮርሶች መውሰዳቸውን ጠቅሰዋል። 

ሰልጣኞቹ በበኩላቸው ውትድርና ህይወትን ሰጥቶ አገርን ማስቀጠል በመሆኑ ለዚሁ ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተለይም በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚጠበቀውን ሀላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም