ለትምህርት ዘርፉ የሚያስፈልገው በጀት ካልተመደበ ብዙ ርቀት ልንጓዝ አንችልም - አፍሪካ ኅብረት - ኢዜአ አማርኛ
ለትምህርት ዘርፉ የሚያስፈልገው በጀት ካልተመደበ ብዙ ርቀት ልንጓዝ አንችልም - አፍሪካ ኅብረት
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ አገራት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ግቦቻቸው እንዲሳኩ የትምህርት ፋይናንስ ምጣኔያቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ የአፍሪካ ኅብረት አሳሰበ።
የአፍሪካ ሕብረት የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም 44ኛውን የሕብረቱን የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ እንዲሁም የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም 37ኛውን የሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ያካሂዳል።
የሕብረቱ ጉባዔ እና የ2024 መሪ ቃል "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት" የሚል ነው።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሐመድ ቤልሆሲን፤ ኮሚሽኑ ትምህርትን የ2024 መሪ ቃል አድርጎ የመረጠበት ምክንያት አፍሪካውያን ለትምህርት ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ በማድረግ በመስኩ ያሉ ችግሮች ላይ በመነጋገር የጋራ መፍትሔ ለማበጀት መሆኑን ለኢዜአ ገልፀዋል።
የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል የተጀመሩ እርምጃዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎች ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች መከሰታቸውን ተከትሎ ሊተገበሩ በታሰቡ ለውጦች ላይ እክል መፍጠሩን አስታውሰዋል።
በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮች የአፍሪካ አገራት በተለያዩ መስኮች ሊያሳኳቸው ባሰቧቸው ግቦች ላይ ተግዳሮት መሆናቸውን አንስተዋል።
ችግሮቹን ለመፍታት አገራት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አንዱን ከአንዱ የማስበለጥ ፈተና ውስጥ በመግባታቸው የትምህርቱ ዘርፍም የዚሁ ሰለባ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርት መስኩ በቀውስ ውስጥ እያለፈ እንደሚገኝና አፍሪካ በዚህ ከፍተኛ ጫና መሸከሟን ነው ፕሮፌሰር መሐመድ የገለጹት።
የአፍሪካ ሕብረት ከአባል አገራትና ልማት አጋሮች ጋር በመሆን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራትን ለማረጋገጥ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በአፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ለትምህርት ብቁ ከሆኑ 500 ሚሊየን ሰዎች መካከል 100 ሚሊየኑ ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸውን አመልክተዋል።
ለትምህርት ጥራት ቁልፍ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የመምህራንን አቅም ማጎልበት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 የተጠቀመጠውን ዓለም አቀፍ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ሽፋን ለማሳካት አሁን ካለው ተጨማሪ ከ15 እስከ 17 ሚሊየን አስተማሪዎች እንደሚያስፈልጉ ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
በአፍሪካ የቅድመ-መደበኛ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥር በሚጠበቀው መልኩ ባይሆንም በዝግታ እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል።
የአፍሪካ መምህራንን አቅም ለማጎልበት ከክፍያ፣ ሥልጠናና ከፖሊሲ ጋር በተገናኘ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ሕብረቱ የአፍሪካ የመማርና ማስተማር ሂደት ከውጭ አገራት የትምህርት አሰጣጥ ተፅዕኖ በማላቀቅ አህጉር በቀል የትምህርት ሥርዓት እንዲቀረጽ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ገበያው ከሚፈልገው የሰው ኃይል ጋር የተጣጣመ ትምህርትና ሥልጠና መስጠት በትኩረት እየሰራባቸው ያሉ ጉዳዮች መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
የአፍሪካ አገራት በትምህርት መስክ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ማሟላት ካለባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) እስከ 15 በመቶ የሚሆነውን ለትምህርቱ ዘርፍ መበጀት ሲችሉ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
የአፍሪካ አገራት ባሉባቸው ተወዳዳሪ ፍላጎቶችና ፈተናዎች አንጻር በትምህርት ዘርፍ የሚጠበቅባቸውን መዋዕለ-ንዋይ እያፈሰሱ አይደለም ነው ያሉት ኮሚሽነሩ።
ይሁንና የአፍሪካ አገራት ለትምህርቱ ዘርፍ የሚመድቡትን ፋይናንስ ማሳደግ ካልቻሉ በዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ርቀት መጓዝ እንደማይቻል አስረድተዋል።
ስለሆነም አገራት ለትምህርቱ ዘርፍ የሚመድቡትን በጀት በማሳደግ ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት አበክረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ለአባል አገራት ፋይናንስን ጨምሮ የፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፎችን የማዘጋጀትና አቅም የመገንባት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ማስፋት ለአጀንዳ 2063 መሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የልማት አጋሮችን ጨምሮ የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ለአፍሪካ ትምህርት እድገትና ልማት አስፈላጊውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።