አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በጨረታ ለሽያጭ ማቅረቡን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ሶስት ሺህ 452 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ ለሽያጭ ማቅረቡን ገለጸ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት እንደገለጹት በአዲስ አበባ የነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ከአቅርቦቱ አንፃር በቂ አይደለም።

የቤት ፍላጎቱን ለማሟላትም ኮርፖሬሽኑ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸው ከለውጡ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት በ60 እና በ90 ቀናት በመንግሥትና የግል ባለሀብቶች ትብብር 35 ሺህ ቤቶች ተገንብተው በዝቅተኛ ኑሮ ለሚተዳደሩ ነዋሪዎች መተላለፋቸውን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በተለያዩ አማራጮች ከ445 ሺህ በላይ ቤቶችን በመገንባት ለነዋሪዎች ማስተላለፍ ተችሏል ነው ያሉት።

በ14 ዙሮች ከ350 ሺህ በላይ ቤቶች ለነዋሪዎች መተላለፋቸውን ገልጸው፤ ከፍላጎት አኳያ ሲታይ ግን በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ከ120 ሺህ በላይ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ለመገንባት ከአልሚዎች ጋር ውል በመዋዋል ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ የገጠመውን የገንዘብ ችግር ለመፍታት የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በፍጥነት በማስተላለፍ 36 ቢሊየን ብር ተመላሽ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ተጨማሪ 37 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ያልተከፈለ እዳ አለበት ብለዋል።

የገንዘብ እጥረቱን በተለያዩ አማራጮች ለመተካት የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በጨረታ ለሽያጭ ሊያቀርብ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት 3 ሺህ 146 የመኖሪያና 306 የንግድ ቤቶች በድምሩ ሶስት ሺህ 452 የመኖሪያና የንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ ለመሸጥ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም