በአፍሪካ ቀንድ ያለውን እምቅ የልማት አቅም ወደ ጥቅም በመለወጥና ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ቀጣናን መፍጠር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በአፍሪካ ቀንድ ያለውን እምቅ የልማት አቅም ወደ ጥቅም በመለወጥና ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ቀጣናን መፍጠር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 25/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን እምቅ የልማት አቅም ወደ ጥቅም በመለወጥና ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ቀጣናን ለመፍጠር የአካባባው ዩኒቨርሲቲዎች ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሀርጌሳና ጅቡቲ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ቀጣናዊ የሰላም ግንባታ፣ ዘላቂ ልማትና አካባቢያዊ አብሮነት ላይ ያተኮረ ኮንፍረንስ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የሰላም ግንባታ አካታች ምክክርንና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የምርምር መፍትሔዎች እንደሚፈለግ ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አህጉራዊና ቀጣናዊ ችግሮችን በመቅረፍ የሰላም ግንባታና የጋራ ልማትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ን ለማሳካት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሶማሌላንድና ጅቡቲ መካከል የጋራ የትብብር ጉዳዮች ላይ የተቀናጀ ስራ ለመስራት የቀጣናው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የማቀናጀትና በጋራ እንዲሰሩ የማድረግ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊና ቀጣናዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እየተጋች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአፍሪካ ቀንድ እምቅ እሴቶችና የልማት አቅሞች ቢኖሩትም ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካባቢውን እምቅ አቅም በምርምር በመለየት የጋራ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ለዚህም በኢትዮጵያ ጅቡቲና ሶማሌንድ መካከል የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ድንበር ዘለል ትብብርን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከይረዲን ተዘራ በበኩላቸው በቀጣናው የሰላም ግንባታንና ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ቀጣናው ግጭቶች፣ የሽብር እንቅስቃሴና ሌሎች ችግሮች የሚታዩበት ሲሆን በተለይም ለድርቅ፣ ጎርፍ እና ለበረሃ አንበጣ ችግሮች ተጋላጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተጠቀሱትን ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት የተረጋጋና በልማት የተሻለ ቀጣናን ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
ለዚህም የቀጣናው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምርምሮችንና ቀጣናዊ ውይይቶችን በማድረግ የፖሊሲ ሀሳቦችን የማቅረብ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የድሬዳዋ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሀርቢ ቡህ፥ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሶማሌላንድ በታሪክና በባህል ጥብቅ ትስስር አላቸው ብለዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለዘመናት የዘለቀውን ትስስር በጋራ ልማት ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል።
ሁሉንም ያካተተ የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊ የሆነና የጋራ የህብረተሰብ ተጠቃሚነት፣ የሰው ኃይል ግንባታና መሰል ጉዳዮች ላይ በምርምር እንዲያግዙም ጠይቀዋል።
ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናከርና የተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር በቅንጅት መሥራት ተገቢ መሆኑን ነው ያነሱት ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባ አደም፥ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጋራ የሆነውን የነገ እጣ ፈንታ ለማሻሻልና የጋራ እሴቶችንና የመልማት አቅሞችን ወደ ጥቅም ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቀጣናውን ለሁሉም ዜጎች የተመቸና የተረጋጋ ለማድረግ በምርምር የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከቀጣናው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በምርምርና መማር ማስተማር ዙሪያ በቅንጅት እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት በትጋት ይሰራል ብለዋል።