ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአቪዬሽን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ደኅንነቱ የተረጋገጠ የአቪዬሽን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ በ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ እንግዶች ደኅንነቱ የተረጋገጠ መስተንግዶ ለማድረግ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ላይ ቅንጅታዊ አመራር ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ገለጸ።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የተቋቋመው ኮሚቴው በይፋ ስራ በመጀመረበት መድረክ ላይ በቅርቡ የሚደረገው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ደኅንነቱ በተረጋገጠ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መስክ ቅንጅት እና ርብርብ በማድረግ ውጤታማ አመራር ለመስጠት አቅጣጫ ተቀምጧል።
የአቪዬሽን ዘርፍ የሴኪዩሪቲ ሥራና ዝግጁነት ሁሌም በንቃት የሚተገበር ቢሆንም ከ12 ዓመታት በኋላ በሰኔ ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ለሚደረግው ሀገራዊ ኦዲት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለሚያደርገው ኦዲት ሁሉም የኮሚቴው አባል ተቋማት አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትብብር ለማድረግ የድርሻ ተግባራትን በመውሰድ በቼክሊስት ክትትል የሚደረግበት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም ተገልጿል።
የኮሚቴ ሰብሳቢና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ሲሳይ ቶላ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የምትጠቀምባቸው አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ኤርፖርቶች አገልግሎትና የአየር ክልል ቁጥጥር በሚመለከት በቅርቡ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በካናዳ እና እስራኤልን ጨምሮ በሌሎች 10 ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኦዲቶችን ያለ ምንም ግኝት ማለፍ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
ነገር ግን በየጊዜው ተለዋዋጭ በሆነው የአቪዬሽን ኢንደስትሪ እና በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎት ውስጥ የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ሥራውን በይፋ መጀመሩ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እና ውሳኔዎችን ለመስጠት እንዲሁም ቅንጅታዊ አመራር ለመዘርጋት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ከመቋቋሙ አስቀድሞ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መሪነት በአቪዬሽን ዘርፉ ተግባራዊ በተደረጉ የሪፎርም ሥራዎች ስር ነቀል ለውጥ በመከናወኑ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ያመለከቱት አቶ ሲሳይ፤ በእነዚህ የሪፎርም ስራዎችም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ 1230 ኪ.ግ የአደንዛዥ ዕፅ፤ በሀገራችን የምንዛሬ ዋጋ ሲተመን 95 ሚሊዮን ብር ገደማ የተለያዩ ሀገራት ሕገ-ወጥ ገንዘብ እንዲሁም 125 ድሮን፣ 428 ባይነኩላር እና ሌሎችም ለታጣቂዎች የሚውሉ የቴክኖሎጂና የስለላ መሳሪያዎች በቁጥጥር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል።
የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ከአቪዬሽን ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እንደ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ ፌዴራል ፖሊስን ፤ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮችን ጨምሮ 10 ተቋማትን በአባልነት ያካተተ ኮሚቴ ነው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አግልግሎት የላከልን መረጃ፤ ለግማሽ ቀን የተካሄደው የብሔራዊ አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ስብሰባ የኮሚቴውን መተዳደሪያ መመሪያ በማጽደቅና የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መጠናቀቁን አመልክቷል። ሀገራችን ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ1944 የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅትን (ICAO)ን በመቀላቀል ከአፍሪካ የመጀመሪያዋ የድርጅቱ ፈራሚ አባል መሆኗን አስታውሷል።