ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሊካሄድ ነው። 

በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽንና በአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በጋራ የሚዘጋጀው ይኸው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ከጥር 29 እስከ የካቲት 5/2016 ዓ.ም ይካሄዳል። 

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ እንደገለጹት በኤግዚቢሽንና ባዛሩ ከ250 በላይ አምራችና ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይሳተፋሉ።

በዚህም ከ400 በላይ የተለያዩ ምርቶች እንደሚቀርቡበት ገልጸዋል።

የተለያዩ አይነት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ሽያጭና የግብርና ምርት የግብይት ዉል የማፈራረም መርኃ ግብር እንደሚካሄድም ነው ያብራሩት። 

ኤግዚቢሽንና ባዛሩ 100 ሺህ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ በቁጠባና በሌሎች ዘርፎች የተደራጁ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይሳተፋሉ ብለዋል።

ይህም የእርስ በርስ ትስስር ለማጠናከርና ለመተዋወቅ የሚያግዝ መሆኑን በመጠቆም። 

የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚያስችል ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም