ቀጥታ፡

በቀጣይ ወር ወደ ሥራ የሚገባው የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ የአገሪቷን የገቢ ወጪ ንግድ በአግባቡ ያሳልጣል

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ በቀጣይ ወር ወደ ሥራ የሚገባው የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ የአገሪቱን የገቢ ወጪ ንግድ በአግባቡ ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተገለጸ። 

የጉምሩክ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።


 

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ጊዜ ኢትዮጵያ በርካታ የገቢና ወጪ ንግድ ያላት ሲሆን ይህ የንግድ ሥርዓት ግን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አይደለም ብለዋል። 

በዚህም የወጪ ገቢ የንግድ እቃዎች ከመነሻቸው እስከ መዳረሻቸው ድረስ በሚኖረው ዝውውር የንግድ ቅልጥፍና መጓደል፣ ቅሸባና ሥርቆት እንዲሁም ሌሎች ችግሮች ሲስተዋሉ የቆዩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላው ዓለም የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ቀድም ብሎ የተጀመረ ሲሆን በኢትዮጵያ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ለረዥም ጊዜያት ጥረት ሲደረግ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበው የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አማካሪነት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በኩል በአገር በቀል እውቀት የለማ መሆኑ ተናግረዋል። 

የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲደረግ ወደ አገር በሚገቡና ወጪ በሆኑ የእቃ ካርጎ ተሽከርካሪዎች ላይ በመግጠም ሁሉንም እንቅስቃሴዎች መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም  ይህ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲሆን  የአገሪቷን የገቢ ወጪ ንግድ በአግባቡ በማሳለጥ ውጤታማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር የላቀ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓቷ ባለመዘመኑ ምክንያት፣ በቅልጥፍናና በጥራቱ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲገጥሙ የቆየ መሆኑን አንስተዋል።


 

በመሆኑም ይህ የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሲደረግ የጭነቶችን ደህንነት በመጠበቅና በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ በመሆን የንግድ እንስቃሴዎችን ለማዘመን ያግዛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የፕሮጀክቱ ማኔጀር አቶ ይታገሱ ደሳለኝ፣ የቴክኖሎጂ ሥርዓቱ የንግድ ሥርዓቱን ከማዘመን ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ውስጥ ያላትን ድርሻ የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል። 


 

የኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ እስከ መጪው የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም