በኦሮሚያ ክልል ከ253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከ253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በ2015/16 ምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነ ከ9 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር ላይ እስከ አሁን 253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ የክልሉ መንግስትን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በኦሮሚያ ክልል በ2015/16 ምርት ዘመን 8 ነጥብ 12 ሚሊየን ሄክታር ለማልማት ታቅዶ 9 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ተናግረዋል።
በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 265 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከአሁን ከ253 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በመስኖ ስንዴ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከ 2 ነጥብ 78 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሽፈኑን ገልጸዋል።
በዚህም 105 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ነው የገለጹት።
በሌላ በኩል አሸባሪው ሸኔ ቡድን የክልሉን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማስተጓጎል ሰሞኑን መንገድ ለመዝጋት የጠራው እገዳ ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት እቅዱን ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ የመደበኛ እንስቃሴውን እንደተለመደው መቀጠሉን ገልፀው፤ ይህንንም ምክንያት አድርጎ በህብረተሰቡ ላይ የታሪፍ ጭማሪ የሚያደርጉ እና አገልግሎት በማይሰጡት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
መንግስት አሁንም ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እና ሰላምን ለማስፈን እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከሰላም አማራጭ ውጪ በሚንቀሳቀሰው ኃይል ላይ የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።