በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይጠናከራሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ ሊያደርጉ የሚችሉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚጠናከሩ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ በአሥር ቀናት ውስጥ በደቡብ ምዕራብና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ከሚስተዋለው አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት በስተቀር በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይቀጥላል ብሏል።
ያም ሆኖ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እንደሚጠናከሩ ጠቁሟል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተለይም በመጀመሪያዎቹ ቀናቶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አስታውቋል።
በተጨማሪም አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በተለይም በምዕራብ መካከለኛውና ደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አመላክቷል።
በእነዚሁ ቀናት ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ የሰሜን፣ የምዕራብና የምስራቅ ሸዋ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙም የትንበያ መረጃዎች መኖራቸውን አስታውቋል።
አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የደቡብና የሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ የባህር ዳር ዙሪያም በተመሳሳይ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸው እንዲሁ።
በተመሳሳይም የሰሜንና የደቡብ ወሎ እንዲሁም የዋግህምራ ዞኖች፣ ከትግራይ ክልል የምስራቅ የመካከለኛውና ደቡብ ምስራቅ ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ የሚኖራቸው መሆኑ ተጠቅሷል።
በጥቂት ሥፍራዎቻቸው ላይም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ በትንበያው አመልክቷል።
ከጋምቤላ ክልል የመዥንግና ጥቂት የአኝዋክ ዞኖች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች ፣የመካከለኛው ጎንደርና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውም ተገልጿል።
የባሌ፣ የምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ እንዲሁም የሀረሪና ድሬዳዋ፣ ከሱማሌ ክልል የሲቲና ፋፈን ዞኖች፣ ከአፋር ክልል ዞን 2 እና ዞን 4 እንዲሁ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።