ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ማዳበሪያ ለማቅረብ እና በሀገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ማዳበሪያ ለማቅረብ እና በሀገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ማዳበሪያ ለማቅረብ እና በሀገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ ።
በአፍሪካ ሩሲያ የመሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሜር ፑቲን የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች የተነጋገሩባቸውን የግብርና ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ በሩሲያ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ሚካሂል ዩሪን የተመራ ልዑካን ቡድን ግብርና ሚኒስቴር ተገኝቶ መክሯል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሶፊያ ካሳ እና ሌሎች አመራሮች ልዑካን ቡድኑን ተቀብለው አነጋግረዋል።
ልዑካን ቡድኑ ሩሲያ ማዳበሪያ ለኢትዮጵያ ማቅረብ በምትችልበትና ማዳበሪያው በአገሪቱ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።
በሁለትዮሽ ውይይቱ የሁለቱ አገራት የማዳበሪያ ግብዓት አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
ኢትዮጵያ በግብርና ሜካናዜሽን እና ማዳበሪያ ማምረቻ ዘርፍ ከሩሲያ ልታገኝ ከምትችለው ልምድና የቴክኖሎጂ ድጋፍ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ ሩሲያ የማዳበሪያ ግብዓትን ለማሟላት ብሎም ለማምረት እያደረገች ያለውን ትብብር አድንቀዋል።
የአርሶአደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት አበክረን እየሰራን ነው ያሉት የግብርና ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች አብራርተዋል።
የሩሲያ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ሚካሂል ዩሪን በበኩላቸው ማዳበሪያ በማቅረብና በማምረት ሂደት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ገልጸዋል።
ሚካሂል ዩሪን ሩሲያ ግዙፍ የማዳበሪያ አምራች መሆኗን ጠቁመው ለኢትዮጵያ ማዳበሪያ የማቅረብና የማምረቱን ተግባር ከዳር ለማድረስ ሁለቱ አገራት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚሁ ተግባር የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ እስከ ሚያዚያ 2016 ድረስ ዝርዝር ተግባራት ተሰርተው እንዲቀርቡ ዶክተር ግርማ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።