ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው ሥምምነት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን አምባሳደሮች ተናገሩ።
ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን ሥምምነት ከሶማሊላንድ ጋር መፈራረሟ ይታወሳል።
በሥምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝ ሲሆን ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያዎች ድርሻ የምታገኝ ይሆናል።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮች ሥምምነቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ከአገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነት መርህን ታስቀድማለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነት የዚሁ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከሱማሊላንድ ጋር የደረሰችው ሥምምነት በጋራ መልማትና የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ነው።
ይህንንም መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ያም ሆኖ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ለዲፕሎማቶች ብቻ የሚተው አይደለም፤ በዚሁ ጉዳይ ዜጎችም ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና የማይሹ አካላት ሥምምነቱ በሌላ መልክ እንዲወሰድ እየተንቀሳቀሱ ነው፤ ይሄ ደግሞ ፈጽሞ አይሳካላቸውም ሲሉም ነው አምባሳደር ዳባ የተናገሩት።
በደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነቢል መህዲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለይም ከጎረቤት አገራት ጋር ያላት ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
ለዚህም ከጎረቤት አገራት ጋር በመሰረተ ልማት ለመተሳሰር የጀመረቻቸው የልማት ፕሮጀክቶች ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የሰጥቶ መቀበል ፖሊሲዋ ነጸብራቅ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ሥምምነትም የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ መሆኑም አመልክተዋል።