ቀጥታ፡

ቲከሻ ቤንጊ- የሰላም፣ የአብሮነትና ልማት እሴቶች ማኅደር

በቀደሰ ተክሌ

በሸኮ ብሔረሰብ ዘንድ ዘመን በልማት ሥራ ይሰፈራል። ምርት ተሰብስቦ አልቆ የጥር ፀሐይ ልምላሜውን ሲያስጎንብስና ቅጠሎችን ካሉበት ቅርንጫፍ ሲያሳሳ አዲስ አመትን ወደ ፊት አንድ ብለው ይቆጥራሉ።

ከፀሐይ መበርታት በፊት በክረምቱ የተዘራው በጓሮና በመስክ ያለው ሁሉ ምርት ወደ ጎተራ ይሰበሰባል። በባህላቸው መሠረት እህል ደረሰ ተብሎ እንዲሁ ለብቻ አይበላም። ከያሉበት ተጠራርተው በአንድነት አዲሱን እህል ቀምሰው አሮጌውን ዘመን በመሻር አዲሱን በአዲስ እህል በአዲስ መንፈስ በጋራ ይቀበላሉ። ይህም በዓላቸው "ቲከሻ ቤንጊ" ይባላል።

ሸኮዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ውስጥ ይገኛሉ። እነርሱ ያለፈው የአዝመራ ምርት ከአራዊት፤ ቤተሰቦቻቸውም ከወረርሽኝና መሰል አደጋዎች ነጻ ሆነው በሰላም ለሚናፍቋት የጥር ወር ሲደርሱ ምስጋናቸው ከፍ ያለ ይሆናል። በቲከሻ ቤንጊ በዓል ሲከበር የብሔረሰቡ ባላባቶች ስለ ትናንት መልካምነት ለፈጣሪ ምስጋና ቸረው ስለ ነገው ተስፋ ልመናና ምርቃት ያቀርባሉ። በቲከሻ ቤንጊ ላይ የታደሙ ሁሉ ምርቃቱን ቆመው ይቀበላሉ።

የሸኮ ብሔረሰብ የሥራ ወዳድነት መገለጫ ከሆኑ እሴቶች መካከል "ቲከሻ ቤንጊ" አንዱ ነው። በጋራ ተሰባስበው ሲበሉና ሲጠጡ አምሽተው፤ ወጣቶች ሌሊቱን ሙሉ በባህላዊ ቀለም ሲጨፍሩ አድረው በነጋታው እንረፍ አልያም የተዘጋጀውን ምግብና መጠጥ ቁጭ ብለን ጨርሰን ማጣጣም አለብን አይሉም። እንደ ነጋ ሰላም አድርግልን ብለው ከቤታቸው ይወጣሉ። የእርሻ መሳሪያዎችን ይዘው ወደ መስክ የመሠማራት ግዴታን በራስ ፈቃድ ይፈጽማሉ። የተመረቀውን ምርቃትና የባላባቶች ልመናን በልባቸው ሰንቀው የግብርና ሥራቸውን ያቀላጥፋሉ።


 

የሸኮ ብሔረሰብ ለእርሻ በሚንቀሳቀስበት ሁሉ ደኖች አይጠፉም። ያለ አስገዳጅ ምክንያት አንዲት ዛፍ መቁረጥ ነውር ተደርጎም ይቆጠራል። ሰው የማይገባባቸው የጥብቅ ደኖች ባለቤቶች ናቸው። ይህ እንዲሁ የመጣ ሳይሆን በብሔረሰቡ ባህላዊ እሴትና ሀገር በቀል እውቀት በተቃኘ የተፈጥሮ ጥበቃ ሥርዓት ያደገ ነው። በዚህ ጥብቅ ደን ውስጥ ገብቶ ዛፍ መቁረጥ በባህላዊ የባላባቶች እርግማን ያስቀስፋል የሚል እምነት በብሔረሰቡ ውስጥ አድሯል። በዚህም ደኑ ተከብሮ ከአካባቢው አልፎ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ደን ሆኖ ተከልሎ ዛሬም ከነውበቱ ይገኛል። ይህም መሠረት ከ"ቲከሻ ቤንጊ" ሥርዓት ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው የብሔረሰቡ ተወላጅ አቶ ጉጂ ከይሳ ይናገራሉ።

የ"ቲከሻ ቤንጊ" የያዘው ሌላውና ትልቁ እሴት ሰላም ነው። ለሰላም ቅድሚያ መስጠትን የሚመክሩበት በአብሮነት መድመቅን የሚያቀነቅንበት ነው። በሸኮ ብሔረሰብ የተጣላ ሰው የቲከሻ ቤንጊ በዓል ታዳሚ መሆን አይችልም። ለዚህም ፍቱን መድኃኒት ባህላዊ እርቅ ነው። በዚህ የእርቅ ሂደት ውስጥ ቂም የለም፤ ቁርሾ መቋጠርና ያለፈን በደል ማሰብ የተወገዘ ነው። አዲስ የፍቅር ህይወት የአንድነት ጉዞ በመከባበር የደመቀ ማኅበራዊ ኑሮ አዲሱን ዓመት ይቀበሉታል። ጎረቤት ከጎረቤት ያለንን ግንኙነት የሚያጠናክርልን በዓል ነው የሚሉት አቶ ጉጂ ሃይማኖት፣ ዘርና ቀለም በቲከሻ ቤንጊ ሥርዓት ውስጥ እንደማይጠየቅ ገልጸዋል። ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ተዛዝኖ ተከባብሮ እንዲኖር የሚያስችል ትውፊት ያለው ነው።

አቶ ቱሪ ኮዛ የሸኮ ወረዳ ሀገር ሽማግሌ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ባህላዊ እሴቶች የማኅበረሰብ ስብዕና ለመገንባት ትልቅ አቅም አላቸው። በቲከሻ ቤንጊ በዓል የሰላም፣ የአብሮነትና የመተጋገዝ እሴት ጎልቶ ይንጸባረቃል። የቲከሻ ቤንጊ በዓል ወርሃ ጥርን ጠብቆ መከበሩ ሰው ሁሉ የአዝመራ ሥራውን ጨርሶ ጥቂት የእረፍት ቀናትን የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል። በዚህ ወር ከሸኮ ማኅበረሰብ ጓዳና ደጅ እህል አይጠፋም። የሚጠጣውም ባህላዊ መጠጥ እንዲሁ በልፋት ከተገኘ የግብርና ምርት ይዘጋጃል። ስለዚህ አርሶ አደሩም ባላባቱም ሐሴት በሚያደርግበት በዚህ የጥር ወር የ"ቲከሻ ቤንጊ" በዓል ተከብሮ ዘመን ይለወጣል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ በዓል በውስጡ የያዛቸውን መልካም ዕሴቶች አሁን ላይ ያለው ትውልድ እንዲያውቀው የማስተማር ኃላፊነትን ከሌሎች የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን እንደሚወጡ ተናግረዋል። ምክንያቱም ከዚህ ቱባ ባህል ውስጥ ወንድማማችነት ይቀዳል፤ ፍቅርና የመተዛዘን መንፈስ ታፍሶ ለሀገር ሰላምን ያውጃልና። በዚህም የሰላም፣ የአንድነትና የልማት እሴቶችን ሳይነጣጥል በማኅደሩ አቅፎ በየዓመቱ ቲከሻ ቤንጊ በሸኮዎች ዘንድ ይመጣል። ይህን እሴት በአግባቡ ማልማት ከተቻለ በህዝቦች የእርስ በእርስ ትስስር ፈጠራ ላይ ጉልህ ሚና እንዳለው በዘርፉ ጥናት ያደረጉት የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነትና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ታደለ ቆንጥር ይገልጻሉ።

በተለይ ሰላምን ለመፍጠር ትልቅ ኃይል ያላቸውን ሥርዓቶች አውጥቶ መጠቀም ዛሬ ላይ እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ላሉ ግጭቶች ፍቱን መድኃኒት ነው ይላሉ። በጥናታቸው እንዳረጋገጡት ብሔረሰቡ ባህላዊ ሥርዓቶች ላይ ያለው አመለካከት ከፍተኛ ነው። ስለዚህም የባላባቶች መመሪያ እና የሥርዓት ደንብ ከምንም በላይ ቅቡልነት አግኝቶ በሁሉም ዘንድ ይተገበራል።

ባህሎች ለሀገራዊ ሰላምና አብሮነት የህዝብ ለህዝብ ትስስር መጠናከር ትልቅ ትርጉም አላቸው። ይህን ትስስር ከፍ አድርገው ከሚያሳዩ ባህሎች መካከል የሸኮ ብሔረሰብ "ቲከሻ ቤንጊ" በዓል አንዱ በመሆኑ ማልማትና ተጨማሪ ጥናቶችን በማድረግ እሴቱን ማጎልበት ይገባል ሲሉም ሀሳባቸውን አጋርተዋል። በበዓሉ አብሮ የመብላትና የመጠጣት፣ እርቅን የማውረድ፣ የተራራቀን የማገናኘት፣ የተቸገረን የመጠየቅ እና በአንድነት ተደስቶ የማዜምን ዕድል ይፈጠራል።

የቲከሻ ቤንጊ አመስጋኝነት የሚያስተምር ነው። ስለተደረገልን ነገር ማመስገን ሰብአዊ ልማድ ነው። ማመስገን ለነገ መልካም ነገር የተስፋ መሠረት ነው። ሸኮዎች አመቱን ቆጥረው በዓመቱ ውስጥ የነበሩ መልካም ነገሮችን እየጠቀሱ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ። ባያመሰግኑ ነገ ይጎድልባቸዋል የሚል እምነት አላቸው። ከምስጋናው ቀጥሎ የመልካም ምኞትና መሻት ልመናም ሳይዘነጋ መቅረቡ ነገን አሻግሮ የማየትና ስለ ነገ ዛሬ አስቦ የመሥራት ባህልን የሚያዳብር ክዋኔ ነው። ይህ ሁሉ ሥርዓት በ"ቲከሻ ቤንጊ" እልፍኝ ውስጥ ታቅፏል።

ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችና ፍልስፍናዎች ባለቤት ናት። በማኅበረሰብ ሞራልና ስብዕና ላይ መሠረታቸውን የጣሉ እሴቶች የኢትዮጵያ እውነተኛ ቀለሞች ናቸው። በውስጣቸው ከመለያየት ይልቅ አንድነት፣ ከጥላቻ ይልቅ ወንድማማችነትና ፍቅር እንዲሁም መከባበርና መደጋገፍን ይዘዋልና።

የዘንድሮ ዓመት የሸኮ ብሔረሰብ የ"ቲከሻ ቤንጊ" የዘመን መለወጫ በዓል ባህላዊ ኩነቶችን አንግቦ ከጥር 17 እስከ 19/2016 ዓ/ም በሸኮ ወረዳ ተከብሯል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም