ቀጥታ፡

በእንስሳት እርባታ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የአርብቶ አደሮች የኑሮ ዘይቤ በተለያዩ አማራጮች ማስፋት ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦በእንስሳት እርባታ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የአርብቶ አደሮች የኑሮ ዘይቤ በተለያዩ አማራጮች በማሰፋት  ዘላቂ የህይወት መሰረት እንዲኖራቸው የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መደረጉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቆላማ አካባቢዎች፣ በእንስሳት፣ ውኃ፣ ማዕድን እና መሬት ኃብት የታደሉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በአካባቢው ድርቅ፤ ጎርፍና መሰል አደጋዎች ሲከሰቱ አርብቶ አደሮቹ ችግሩን በቀላሉ መቋቋም እያቃታቸው ከመኖሪያ ቀያቸው የሚሰደዱበት አሳዛኝ ታሪክ ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከለውጡ በኋላ የአርብቶ አደሩን ህይወት በመሰረታዊነት ለመቀየር የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ልማት ፖሊሲ በ2012 ዓ.ም ጸድቆ፤ ፖሊሲውን የሚያስፈጽም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

የአርብቶ አደሩን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የአካባቢውን ጸጋዎች ማዕከል ያደረገ የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ መርሃ ግብር ተቀርፆ ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በቆላማ አካባቢዎች ውኃን ማዕከል በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ተስፋ የሆኑ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የአርብቶ አደሮችን የኑሮ ዘይቤ መሰረት ያደረጉ እንደ ጤና ተቋማት፣ የገበያ ማዕከላትና የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች በስፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የከርሰ ምድርና የዝናብ ውኃን ለእንስሳትና ለህብረተሰቡ የመጠጥ አገልግሎት ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የውሃ ሃብቱን ለመስኖና ለግጦሽ መሬት ልማት ማዋሉን  ተናግረዋል፡፡

በእንስሳት እርባታ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የአርብቶ አደሮች የኑሮ ዘይቤ በተለያዩ አማራጮች በመተካት ዘላቂ የህይወት መሰረት እንዲኖራቸው ይደረጋልም ነው ያሉት፡፡

የማር ምርት፣ ንግድ፣ መስኖ ልማት እና ሌሎች ጸጋዎችን ታሳቢ ያደረጉ አማራጭ የኑሮ መሰረቶች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል ፡፡

ቆላማ አካባቢዎች በመሰረተ ልማት ዝርጋት ከሌሎች አንፃር ወደ ኋላ የቀሩ መሆናቸውን የገለጹት ዶክተር እንድሪያስ፤ የአካባቢዎችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የመሰረተ ልማትና ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በሰባት የቆላማና አርብቶ አደር ክልሎችና መቶ ወረዳዎች እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገና አርብቶ አደሮች ችግር ሲገጥማቸው ፈጥነው የሚወጡበትን አቅም ማጎልበት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም