ቀጥታ፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መከረ

 አዲስ አበባ ፤ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦የጉምሩክ ኮሚሽን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂ አተገባበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መምከሩን   አስታወቀ።

የጉምሩክ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ  ቀደም ሲል  ኤሌክትሪካል ካርጎ ትራኪንግ ቴክኖሎጂን ለመተግብር   የተደረጉ ጥረቶች   አለመሳካታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ  አሁን ላይ  ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ደረጃ ላይ  መደረሱን አንስተው  ለተግባራዊነቱ  ጥረት ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው ይህ ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል ብለዋል፡፡

የዚህ ቴክኖሎጂ በሃገራችን ተግባራዊ መደረግ የጭነቶችን ደህንነት በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


 

በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ ፣የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈውበታል፡፡

ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተሊጀንስ አማካይነት የበለጸገ መሆኑም በውይይት መድረኩ ላይ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም