አለም ባንክ ማህበራዊ ጥበቃ ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2016 (ኢዜአ)፦ አለም ባንክ ማህበራዊ ጥበቃ ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጡን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በአለም ባንክ የአፍሪካ አካባቢ የማህበራዊ ጥበቃና ስራ አተገባበር ስራ አስኪያጅ ሮበርት ቼዝ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁርያ አሊ መንግስት የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት በተለይም ደሃና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው ውሎና አዳራቸው ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች ቁጥር እና ተያያዥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ማህበራዊ ትስስርንና የቤተሰብ ሚና ማሳደግ፣ ማህበራዊ ጥበቃን በዘላቂነት ፋይናንስ ማድረግ የሚኒስቴሩ አላማና ራዕይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ውጤታማ የማህበራዊ ዋስትና ሽፋንን ማስፋፋት ዜጎች ክብራቸው ተጠብቆ የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ መፍጠርም እንዲሁ፡፡

ደሃና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እንደ አለም ባንክ ካሉ ድርጀቶች ጋር ዘላቂ የሆነ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል፡፡

የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለመገንባት እየተሰሩ ላሉ ስራዎች ውጤታማነት የሚረዱ ተጨማሪ ድጋፎች እንደሚያስፈልጉትም መግለጻቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በአለም ባንክ የአፍሪካ አካባቢ የማህበራዊ ጥበቃና ስራ አተገባበር ስራ አስኪያጅ ሮበርት ቼዝ በበኩላቸው አለም ባንክ ህዝብን ያማከለ አካሄድ በመከተል በመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና እና የተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ችግሮች በመፍታት ላይ ያተኮረና የረጅም ጊዜ የልማት እቅድን ይዞ መቅረቡንም ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የአለም ባንክ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎች የሚሰጠውን ማህበራዊ አገልገሎት በዲጂታል መልክ ለማድረግ እንዲሁም አሰራሩን ለማዘመን የሚሄድበትን መንገድ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም