ቀጥታ፡

ጀስዊት (እየሱሳውያን) በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያስቃኝ መጽሐፍ ለንባብ በቃ

አዲስ አበባ ፤ጥር 24/2016 (ኢዜአ) ፦ካናዳዊያን ጀስዊት (እየሱሳውያን) ማኅበር በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያስቃኝ “ስፕላሽ ኦፍ ዳይመንድ” የተሰኘ በእንግሊዘኛ ቋንቋን የተጻፈ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል።

መጽሐፉ የተጻፈው የሃይማኖት አባትና ጣሊያን በሚገኘው የእየሱሳውያን ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ባልደረባ በሆኑት ፌስቶ ምኬንዳ ነው።

የመጽሃፉ ደራሲ ፌስቶ ምኬንዳ፤ በመጽሐፉ በዓለም አቀፉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እውቅና የተሰጠው  የእየሱሳውያን ማኅበር በኢትዮጵያ በተለይም በትምህርት ዘርፍ ያበረከተውን አስተዋጽዖ በስፋት ይዳስሳል ብለዋል።  

በተለይም ማኅበሩ በኢትዮጵያ የትምህርት መጽሐፍት እንዲታተሙና የተለያዩ የትምህርት መርኃ ግብሮች ተቀርጸው በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲካተቱ ያከናወናቸው ተግባራትን አመላክቷል። 


 

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ በበኩላቸው መጽሃፉ ጀስዊት (እየሱሳውያን) ማኅበር በኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ ያላችው ተሳትፎ በምን መልኩ እንደጀመረ ያትታል ብለዋል። 

የጀስዊስት ማኅበር በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ውስጥ የተለያዩ የትምህርት ሥርዓቶችን በመቅረጽ ተማሪዎች በተለይም በሙያዊ ክህሎቶች ዳብረው እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንደቆዩም ያሳያል ብለዋል። 

በዚህም በመጽሐፉ የጀስዊት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት መርኃ ግብሮች እንዲዳብሩ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ ታሪካዊ ዳራን በማጣቀስ አሁን ድረስ ያላቸውን ሚና የሚያስቃኝ ነው ብለዋል።


 

በመጽሃፋ ምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩላቸው ካናዳውያን ጀስዊቶች ለአገሪቱ የትምህርት ዘርፍ ላይ ያበረከቱት አስተዋጽኦ በመጽሃፍ መልኩ መሰነዱ የሚበራታታ ነው ብለዋል።

መጽሓፉ በስድስት ምዕራፍ የተከፋፈለ ሲሆን 146 ገፆች አሉት።   

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም