ቀጥታ፡

የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ ተማሪዎችን ብቁና ተወዳዳሪ ያደርጋቸዋል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ቦንጋ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ፤ ተማሪዎችን ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ምቹ መደላድልን እንደሚፈጥር የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ዛሬ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለቦንጋ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳመለከቱት፤ የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራሉ።


 

የሀገር መሪዎችን ጨምሮ በሁሉም መስክ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት እንዲቻል በቁሳቁስና በቴክኖሎጂ የተደራጁ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሚኒስቴሩ በ2016 በጀት ዓመት በተለያዩ አካባቢዎች ስድስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ መያዙንና የቦንጋውም የዚህ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቶቹ በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን አወዳድረው እንደሚቀበሉም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ስብራትን ለመጠገን ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ የሆነው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ግንባታ ትምህርት ሚኒስቴር ላደረገው አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

አካባቢው በትምህርት መሰረተ ልማት ወደ ኋላ የቀረ መሆኑን አንስተው፣ የአዳሪ ትምህርት ቤት ችግሩን ከማቃለል ባለፈ፤ በርካታ ምሁራንን ማፍራት እንደሚያስችልም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማስጠበቅ በተደረገ ''የትምህርት ለትውልድ'' እንቅስቃሴ ወደ 262 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት በመሰብሰብ የመማሪያ ክፍሎች ጥገናና የትምህርት ቤቶች ግንባታ ማከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ህብረተሰቡም በባለቤትነት ስሜት እገዛ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

''በትምህርት ለትውልድ'' መርሃ ግብር ከዞኑ ሕዝብ በተገኘ 110 ሚሊዮን ብር ትምህርት ቤቶችን የማሻሻልና የመጻህፍት ኅትመት እየተከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የቦንጋ ከተማ ነዋሪው አቶ በላቸው ገብረሚካኤል በሰጡት አስተያየት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በአካባቢያቸው መገንባቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው አመልክተው፣ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

 

በከተማው የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ታለ ተክሌ በበኩሉ የትምህርት ቤቱ መሰረተ ድንጋይ መቀመጡ እንዳስደሰተው ገልፆ፣ በቀጣይ በርትቶ በመማር በትምህርት ቤቱ ዕድሉን ለማግኘት ተስፋ ሰንቄያለሁ ብሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልሉና የዞን ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም