የጌዶኦ አባቶች ለዓለም ያበረከቱትን ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የመኖር ባህላዊ ጥበብ ለማስቀጠል አበክረን እንሰራለን- አቶ ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጌዶኦ አባቶች ለዓለም ያበረከቱትን ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የመኖር ባህላዊ ጥበብ ለማስቀጠል አበክረን እንሰራለን- አቶ ጥላሁን ከበደ
ሀዋሳ ፤ጥር 23/2016 (ኢዜአ)፦ የጌዶኦ አባቶች ለዓለም ያበረከቱትን ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የመኖር ባህላዊ ጥበብ ለማስቀጠል አበክረን እንሰራለን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ አስተዋጾ ላበረከቱ አካላት ዛሬ የዕውቅና መርሀ ግብር በጌዴኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ወረዳ ተካሂዷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን እንዳሉት፣ የጌዴኦ ህዝብ በባሌ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዐት ውስጥ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ፀጋን ጠብቆና ተንከባክቦ ማቆየት የሚችልበትን ሥርዐት በመዘርጋት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዓለም እንዲማርበት ያደረገ ነው።
የጌዴኦ አባቶች በዚህ ባህላዊ ሥርዓታቸው የሰው ልጅ እንዴት ከተፈጥሮ ጋር በወዳጅነት የሚኖርበትን ጥበብ ማኖራቸውን ገልጸው፣ ይህንን ጥበብ ለማስፋትና ለማስቀጠል የክልሉ መንግሥት አበክሮ ይሰራል ብለዋል።
በተለይ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፌዴራል ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች ተግተው በመስራት የጎላ አስተዋጾ በማድረጋቸው አመስግነዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ መመዝገቡ ኢትዮጵን ከአፍሪካ ሀገራት ግንባር ቀደም አድርጓታል ብለዋል።
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት አዳዲስና ነባር ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን የማልማት፣ የማስተዋወቅ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስምና ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች እንዲበራከቱ በማድረግ ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሚኒስቴሩ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች በአግባቡ ለምተውና ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ እንዲተዋወቁና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ቀጣይነት ያለው ሥራ እንደሚያጠናክርም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ሐይሉ በበኩላቸው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዐ ምድር በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ 10ኛው የኢትዮጵያ የሚዳሰስ ቅርስ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርሱ የተመዘገበው የጌዴኦ አባቶች በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘዴ ጠብቀው በማቆየታቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
ይህ ቅርስ የጌዴኦን ህዝብ የጥንት ሥልጣኔ አሻራ የያዘ መሆኑን ገልፀው፣ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ 10 ሺህ ትክል ድንጋዮች ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑት በጌዴኦ ዞን እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ዱባለ ቅርሱ በዩኔስኮ በጊዜያዊ መመዝገቢያ ሰነድ “ቴንታቲቭ ሊስት” ከተመዘገበበት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 11 ዓመታት በየደረጃው ባሉ ባለድርሻ አካላት ፅናትን የሚጠይቁ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
መልክዓ ምድሩ በ29 ሺህ 601 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ በውስጡ ጥምር ደን ግብርና፣ የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ፣ የድንጋይ ላይ ሥዕሎች፣ በዕምነት የተጠበቁ ደኖችና ጥብቅ መካነ መቃብርን ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው የጌዴኦ ህዝብ ለዓለም ያበረከተው ባህላዊ መልክዐ ምድርን በውስጡ የያዘው የባሌ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዐት እስካሁንም ህዝቡ እየተገለገለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ህዝቡ አሁንም ከጥምር እርሻ ጋር በማያያዝ ዓለም አቅፍ እውቅናን ያተረፈውን ይርጋ ጨፌን ቡና ማምረት እንዳለበት ጠቁመው፣ ይህም መልክዐ ምድሩ ቅርስ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አስታዎጾውን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ ከዩኔስኮ የተላከ የምስክር ወረቀት ርክክብ የተደረገ ሲሆን ለቅርሱ መመዝገብ አስተዋጽዖ ያበረከቱ የተለያዩ አካላትም ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።