የዘንድሮ የሐጅ ጉዞ ምዝገባ ጥር 25 ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮ የሐጅ ጉዞ ምዝገባ ጥር 25 ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016 (ኢዜአ)፡-የ1 ሺህ 445ኛ ዓመተ-ሒጅራ የሐጅ ጉዞ ምዝገባ ጥር 25 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ።
ምክር ቤቱ የሐጅ ጉዞ ምዝገባ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ፤ ለ1 ሺህ 445ኛ ዓመተ-ሒጅራ የሐጅ ምዝገባ ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሸኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በሰጡት መግለጫ፤ ምዝገባው በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።
ምዝገባው በመላ አገሪቱ በሚገኙ 27 ማዕከላት እንደሚጀመር ገልጸው፤ ከዚህም ውስጥ ዘጠኝ በዘንድሮ ዓመት የጀመሩ አዲስ ጣቢያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሐጅ ጉዞ ክፍያ 329 ሺህ ብር መሆኑን ጠቁመው፤ የዋጋ ተመኑ ባለበት ፀንቶ የሚቆየው የዶላር ዋጋ አሁን ባለበት ወይም በመደበኛው የአጨማመር ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
ለሐጅ ጉዞ ለመመዝገብ የሚፈልግ ሰው የቀበሌ መታወቂያ፣ የመጠቀሚያ ጊዜው ለመጠናቀቅ ከ11 ወራት በላይ የቀረው ፓስፖርት፣ አንድ ጉርድ ፎቶግራፍ እና የኮቪድና የቢጫ ወባ ክትባት ካርድ ማሟላት ይጠበቅበታል ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት የተሳካ የሐጅ ጉዞ መደረጉን አስታውሰው፤ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።
በዘንድሮ ዓመትም በሚደረገው ምዝገባና ጉዞ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።