ቀጥታ፡

ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት የሚላከው ቡና ኅብረቱ ባወጣው ሕገ-ደንብ መሰረት ለማከናወን እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት የሚላከው ቡና ኅብረቱ ባወጣው አሰራር መሰረት ቡና ለመላክ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ገለጸ።  

የአውሮፓ ኅብረት ቡናን ጨምሮ ወደ አባል ሀገራቱ የሚላኩ ሰባት የምርት ዓይነቶች ከደን ጭፍጨፋና መመናመን ነጻ መሆናቸው ሳይረጋገጥ ለግብይት እንዳያቀርቡ የሚከለክል ሕገ-ደንብ አውጥቶ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀዱ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣንም በኢትዮጵያ የሚካሄደው የቡና ምርት ለአከባቢ ጥበቃና ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ፖሊሲ ከኅብረቱ ፖሊሲ ጋር ታጣጥማለች ብሏል። 

ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣኑ የአውሮፓ ኅብረት ካወጣው ሕገ-ደንብ ጋር የሚናበብ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለው የሦስት ዓመት የአፈጻጸም መርኃ ግብር ማዘጋጀቱን ነው የባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ የሚናገሩት። 

ይህን ለማሳካትም    የባለድርሻ አካላት    መወያየት   እስፈላጊ በመሆኑ የዛረየው ውይይት ግብአት  እንደሚሆን ተናግረዋል።  

በተዘጋጀው የአፈጻጸም በመርሃ ግብር መሰረት የኢትዮጵያ የቡና ምርት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ በሆነ መልኩ በመመረት ላይ መሆኑን የማረጋገጥና የመለየት ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  

  በመቀጠልም የመረጃ ማዕካላትን የማደራጀት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመው በረጅም ጊዜ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎች ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።   

ኢትዮጵያ የቡና ምርት ለአከባቢ ጥበቃና ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ፖሊሲ ከኅብረቱ ፖሊሲ ጋር የማጣጣም ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። 

በውይይት መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባለድርሻ አካላት ኅብረቱ ያወጣውን ሕገ-ደንብ ተግባራዊ በማድረግ ወደ አውሮፓ አገራት የሚላክ የቡና ምርትን ለመጨመር እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና የአውሮፓ ኅብረቱ ያወጣውን ሕገ-ደንብ  ለመተግበርና የወጣውን የአፈጻጸም መርሃ ግብር መሬት ለማስያዝ በእሴት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉ የሚመለከት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንሰራለን ብለዋል።  


 

የኦሮሚያ ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ፕሬዝዳንትና ቡና አልሚ የሆኑት አቶ ፈጠነ የኋላእሸት በበኩላቸው ለቡና አምራች አባሎቻቸው ሕገ-ደንቡን በማስረዳት ቡናን ከደን ጭፍጨፋ ውጪ እንዲያመርቱ የማስረዳት ሥራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕገ-ደንብ ለመተግበር የወጣውን የአፈጻጸም መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የተጠቀሰ ሲሆን ይህንንም ከአጋር አካላት ለማግኘት መታቀዱን በዚሁ ወቅት ተጠቁሟል። 

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጪ አገር 117 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 571 ሚሊየን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም