ቀጥታ፡

ኢዜአ ያስገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ የሀገር ገጽታ ግንባታ እና ብሄራዊ መግባባት የመፍጠር ሚናውን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው-የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢዜአ ያስገነባው የተደራጀ ሚዲያ ኮምፕሌክስ በሀገር ገጽታ ግንባታ እና ብሔራዊ መግባባት ላይ እያደረገ ያለውን ሚና ይበልጥ እንደሚያጠናክር   የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት አመራሮች አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ የ82 ዓመታት ዕድሜ ባለጸጋው ኢዜአ አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ በተሟላ ሁኔታ መደራጀቱን አድንቀዋል።

ኢዜአ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም መረጃን ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የሀገር ባለውለታ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ዘመኑን በዋጀ አግባብ የተደራጀው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ደግሞ ለተቋሙ ትልቅ እምርታ ነው ብለዋል።

ሀገር የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ኢዜአም እየተገበረ መሆኑን ገልጸው፣ ለመጪዎቹ ረጅም ዓመታት በአስተማማኝነት ኢትዮጵያን ማገልገል በሚያስችለው  ቁመና ላይ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ገልጸዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አሠገደች ታደሠ፥ ኢዜአ በቴክኖሎጂ የተሟላ መሆኑ የኢትዮጵያን ጸጋዎች ለማሳየትና ሀገራዊ ገፅታን ለመገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል።

አስተማማኝ የመረጃ ምንጭነቱን በማስቀጠል በማህበራዊ የትስስር አውታሮች የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለመመከት እንደሚያግዘውም ጠቁመዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሊድ አልዋን፥ ኢዜአ በ80 ዓመታት ውስጥ አልፎ ሀገር በሚመጥን ደረጃ መደራጀቱን ጠቅሰው፣ ይህም ትልቅ ስኬት እንደሆነ አንስተዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የሲቪል ባህል ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ፓል ቱት በበኩላቸው የሚዲያ ኮምፕሌከሱ ሀገራዊ ልማትን ለማፋጠን፣ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማስተዋወቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርለት ነው ያነሱት።


 

በተመሳሳይ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የፖለቲካ አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ አህመድ፥ ኢዜአ በቴክኖሎጂ መደራጀቱ ፈጣንና ጥራት ያለው መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

የፓርቲ አመራሮቹ አክለውም አዲስ ያስገነባውን የሚዲያ ኮምፕሌክስ በመጠቀም ተልዕኮውን የማሳካት ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በሀገር ገጽታ ግንባታ እና በብሔራዊ መግባባት ጠንካራ ስራዎቹን ይበልጥ ማጠናከር፣ ሀገራዊ ለውጡን  ለማሳካትም በአጀንዳ መምራት እንደሚጠበቅበት ነው ያነሱት።

ኢዜአ ለትውልድ የሚተርፍ ተቋም እያደራጀ መሆኑን በመግለጽ፤ የጀመረውን ሪፎርም ማስቀጠል፣ የክልል ቅርንጫፎቹን ይበልጥ ማጠናከርና በውጭ ቋንቋዎች ተደራሽነቱን ማስፋት እንዳለበትም አንስተዋል። 

ኢዜአ አስተማማኝ የዜና ምንጭ ከመሆኑ አኳያ የመንግስት እና የግል ተቋማት እና ግለሰቦች መረጃ የሚያገኙበት በመሆኑ ሊገለገሉበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የመንግስት አመራሮችም መረጃን ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ኢዜአን ቀዳሚ አድርገው እንዲጠቀሙበት ነው ያመላከቱት።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም