ቀጥታ፡

ኢዜአ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን አጀንዳዎች ለዓለም በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን አቅም ፈጥሯል- ሁሪያ አሊ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢዜአ የኢትዮጵያንና የአፍሪካን አጀንዳዎች ለዓለም በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ የሚያስችለውን አቅም መፍጠሩን የኢዜአ የስራ አመራር ቦርድ አባልና የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ተቋሙን በአዲስ የከፍታ ምዕራፍ የገለጠ ነው ብለዋል።

 ኢዜአ ላለፉት 82 ዓመታት የኢትዮጵያውያን ድምፅ በመሆን ያገለገለ የሀገር ባለውለታ ተቋም እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢዜአ በሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠርና በዓለም መድረክ የሀገርን ገፅታ የመገንባት ተልዕኮ ይዞ እየሰራ ሲሆን፥ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ይህን ለማሳካት የሚያግዝ ለውጥ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ማሟላቱንና በሰው ኃይል አደረጃጀት ራሱን ማዘጋጀቱን ነው የጠቆሙት።

ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ተልዕኮውን ለማሳካትም በሀገሪቱ ሊካሄድ ዝግጅት እየተደረገበት ለሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ስኬት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አንስተዋል።

ኢዜአ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ላይ የጀመራቸውን ተግባራት አድንቀው፥ ያስገነባው ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ዘመኑን የዋጀና የተቋሙን የአገልግሎት አድማስ የሚያሰፋ ነው ብለዋል።

ይህም አስተማማኝ የዜና ምንጭነቱን በጥራትና በፍጥነት እንዲያረጋግጥና ተደራሽነቱን እንዲጨምር የሚያስችለው ስለመሆኑ በመጥቀስ። 

ኢዜአ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በተቀረው ዓለም ሀገራዊና አህጉራዊ አጀንዳዎችን ተደራሽ የማድረግ ከፍተኛ አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በሀገር ውስጥ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽነት አጠናክሮ ለመቀጠል መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። 

ኢዜአ የሀገርና የአህጉርን ገፅታ የመገንባት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ሁሉም ሰራተኛና አመራር በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም