የተፋሰስ ልማትና የግብርና ሥራዎችን በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
የተፋሰስ ልማትና የግብርና ሥራዎችን በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ጠምባሮ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የተፋሰስ ልማትና የግብርና ሥራዎችን በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የ2016 ዓ.ም የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ዛሬ በጠምባሮ ልዩ ወረዳ በይፋ ተጀምሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ እንደስታወቁት በዓለም አቀፍና በሀገር ደረጃ የተከሰተውን የአየር ንብረት ለውጥ ከግምት በማስገባት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተደራጀ አግባብ እየተከናወነ ይገኛል።
በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው ህብረተሰቡን በማነቃነቅ ጥራት ያለው ሥራ በዘላቂነት ለማከናወን ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
በተለይ የተፋሰስ ልማት ሥራን ከግብርና ልማት ሥራዎች ጋር በማስተሳሰርና ተደጋጋፊነት ባለው መልኩ በመተግበር የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሀገር ባለፉት አራት ዓመታት በምግብ ራስን ለመቻል በተከናወኑ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ፕሮፌሰር ኢያሱ አስረድተዋል።
በተለይ በበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በዚህም የልማት እንቅስቃሴ የአገሪቱን የስንዴ ፍላጎት መሸፈን እንደተቻለ የገለጹት ፕሮፌሰር ኢያሱ፣ በምግብ ራስን ለመቻል በተከናወኑ ሥራዎች በተገኘው ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ማግኘቱን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዘርፉ ለሰጡት ጠንካራና በሳል አመራር ከተባበሩት መንግስታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) በቅርቡ ሽልማት ማግኘታቸውንም አመልክተዋል።
ለስኬቱ የተሰማቸው ደስታ በመግለጽ ለተጨማሪ ውጤት የሚያነሳሳ መሆኑን አመልክተዋል።
"ሽልማቱ ሀገራችን የጀመረችው የልማት ፖሊስን ትክክለኛና አዋጭነት የሚያሳይ በመሆኑ ልማቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉም አረጋግጠዋል።
ለውጤቱ መገኘት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ስራ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ጠቅሰው፣ ዘንድሮም እንደ ሀገር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራውን በማጠናከር ስኬቶችን ለማስቀጠል እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው እንዳሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሀገራችን የተሰጠው እውቅና ተጨማሪ መነሳሳት የሚፈጥር ነው።
የግብርናውን ዘርፍ የኢኮኖሚ ዋስትና ለማድረግ የተወሰደው ቁርጠኛ አቋምና ትኩረት ያስገኘው ውጤት መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ክልሉ የበኩሉን ለመወጣት ተግቶ ይሰራል ብለዋል።
በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል የሚደረገው ጥረት ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው በየዓመቱ ሳይቋረጥ በተቀናጀ መንገድ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዛሬ የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ሥራ ለተከታታይ 25 ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዚህም ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ልማቱ እንደሚከናወን ተመላክቷል።