ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት ዋጋ የምትከፍል እንጂ ስጋት የምትፈጥር አይደለችም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት ዋጋ የምትከፍል እንጂ ስጋት የምትፈጥር አይደለችም
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት ዋጋ የምትከፍል እንጂ ስጋት የምትፈጥር ሀገር አለመሆኗን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማሕዲ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በጋራ የመልማት እንጂ የልዩነት መነሻ አይደለም ያሉት ደግሞ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አብርሃም አረፈዓይኔ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በቅርቡ ለብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖር ትብብር ቀዳሚ መርኋ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራና ሌሎች ጎረቤቶቿ ጋር የትብብር፣ በጋራ የመልማትና ህልውናዊ ቁርኝት አላት ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ስታነሳ ከኤርትራ ጋር ሊዋጉ ነው የሚሉ አካላት እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሶማሊ ላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሲፈረም ደግሞ የጦርነቱን አጀንዳ እያስተጋቡ መሆኑን አንስተዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ሶማሊያ በህዝብ ለህዝብ፣ በባህል፣ በቋንቋና በታሪክ የተሳሰሩ የሁለት ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሁለቱ ሀገራት የቆየ ጠንካራ ግንኙነትና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አንስተዋል።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ አብርሃም አረፈዓይኔ፤ ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘመንና የመንግስት ስርዓት የሌላ ሀገርን ሉዓላዊነት የመዳፈርና የመጉዳት እንቅስቃሴ አድርጋ አታውቅ፤ አሁንም አታደርግም ነው ያሉት።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት እንቅስቃሴ መጀመሯ ሌሎችን የመጉዳት ሳይሆን አብሮ የመልማት ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና ደህንነት ስትል ወታደሮቿን በማሰማራት አልሸባብን እየተፋለመች ስለመሆኗም ገልጸዋል።
የሶማሊያ መንግስትና አንድነት የቀጠለው በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ውድ የህይወት መስዋእትነት ጭምር መሆኑን አለም የሚያውቀው ሃቅ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነትም ማንንም የመጉዳት ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ የመልማት መሆኑን ዶክተር ፈትሂ ገልጸዋል።
በመሆኑም የተደረሰው የባህር በር ስምምነት በሶማሊያ አንድነት ላይ የተቃጣ ስጋት በማስመሰል የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ተገቢነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሊያ ያላቸው መልካም ግንኙነት የላቀ መሆኑን ጠቅሰው የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ አንድነት ሲሉ እየከፈሉት ያለው መስዋእትነትም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የመልማት ጉዞ እና ከፍታ የማይፈልጉ አንዳንድ አካላት ፍትሐዊ የባህር በር ጥያቄዋን አዛብተው ውዥንብር እየፈጠሩ መሆኑን ዶክተር ፈትሂ አንስተዋል።
በመሆኑም የነዚህ አካላት ፍላጎት ቀጣናው የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ሆኖ እንዲቀጥል መሆኑን የአካባቢው ሀገራት በቅጡ ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ማስከበር የከፈለችውን ዋጋ በመጥቀስ አብሮ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነት አላማ እንጂ የመጣላት ፍላጎት እንደሌላት መግለጻቸው ይታወቃል።
የሶማሊያን አንድነት ለማጠናከር የተለያዩ ጥረቶች ማደረጉንም ገልፀው፤ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ችግር ይፈጠራል ብለው እንደማያስቡና ጉዳዩን በተረጋጋ መንገድ ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፍላጎት የባህር በር ማግኘት ብቻ መሆኑን በአፅንኦት ጠቅሰው ይህንንም በሳል ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ተፈጻሚ እናደርገዋለን ነው ያሉት።