የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ስድስት ወራት ከ514 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ባለፉት ስድስት ወራት ከ514 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ514 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ።
ኢንተርፕራይዙ ገቢውን የሰበሰበው የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ከክፍያ መንገድ አገልግሎትና ከልዩ ልዩ ገቢዎች መሆኑን ገልጿል።
በመጀመሪያ 6 ወራት ከታክስ በፊት 271 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን ይህም ከባለፈዉ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 27 ነጥብ 8 በመቶ የትርፍ እድገት ማስመዝገብ ችሏል።
የኢንተርፕራይዙ የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዉ ስድስት ወራት የትርፍ አፈፃፀም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 111 በመቶ መሆኑም ታውቋል።
የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአሁኑ ወቅት ሦስት የክፍያ መንገዶችን (አዲስ አበባ-አዳማ ፣ ድሬደዋ-ደወሌ እና ሞጆ-ባቱ) እያስተዳደረ በየዕለቱ ከ29 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የክፍያ መንገድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።