የቆዳ ምርትን ለመጨመር ታስቦ የወጣው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ ባለመሆኑ የምርት ምጣኔው ላይ ጫና አሳድሯል - ኢዜአ አማርኛ
የቆዳ ምርትን ለመጨመር ታስቦ የወጣው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ ባለመሆኑ የምርት ምጣኔው ላይ ጫና አሳድሯል
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ የቆዳ ምርትን ለመጨመር ታስቦ የወጣው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ ባለመሆኑ የምርት ምጣኔው ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ገምግሟል።
በዚሁ ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል የተቋሙን የግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ፣የወጪና ተኪ ምርት መጠንንና ገቢን ማሻሻል፣ የኢንቨስትመንት ዕድል መሳቢያ አማራጮችን ማስፋትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሪፖርቱ ያካተታቸው ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው።
ባለፉት ስድስት ወራት የአምራች ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ላይ በተከናወኑ ተግባራት 6 ነጥብ 7 ሚሊዬን ቶን ግብዓት ቀርቧል፡፡
አፈጻጸሙ ባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ከቀረበው 6 ነጥብ 6 ሚሊዬን ቶን በ 83 ሺ 612 ቶን ወይም የ1 ነጥብ 26 ብልጫ አሳይቷል ብለዋል ።
የወጪና ተኪ ምርት መጠን ማሻሻል ላይ በተሰራ ስራ 1 ነጥብ 3 ሚሊዬን ቶን የምግብ፣ መጠጥ፣ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት የቀረበ ሲሆን ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ 252 ሺህ ቶን ጭማሪ አሳይቷል።
ይሁን እንጂ ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች የሚቀርቡ ግብዓቶች በአግባቡ ተደራሽ አለመሆናቸው ዘርፉ በሚጠበቀው ልክ እንዳያድግ ማነቆ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በጨው ሃብት ላይ ለሚነሱ የባለቤትነት ጥያቄዎች ህጋዊ አሰራርን በተከተለ አግባብ ምላሽ ለመስጠት መመሪያዎች ቢወጡም አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከመቀነሱ ባሻገር በቂ የስራ ዕድል እንዳይፈጠር ማድረጉን ነው ያስረዱት ።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርት እጥረት የሚከሰትባቸውን ጉዳዮች በመለየት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር ሚኒስቴሩ በትኩረት እንዲያየው ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት፣ ቴክኖሎጂያዊ አሰራርና መሰል የመሰረተ ልማት ስራዎችን በማሟላት ረገድ ክፍተቶች እንዳሉ በመጠቆም ችግሩን ለማቃለል የተከናወኑ ተግባራት ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ጥያቄ አቅርበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ድኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ከቋሚ ከሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የተነሱት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ተቋሙ አሰራሩን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በተለይም አምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ማነቆዎች በመፍታት ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ዘርፉን ስኬታማ ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አማረች በጋሎ ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እያከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማስፋፋት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገሪቱ ያላትን የማምረት አቅም በተግባር ያሳየ በመሆኑ ዘርፉ የሚያድግበትን አማራጭ በማስፋት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን ማጉላት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።