ቀጥታ፡

የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ለማልማት የሚውል የ28 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) ጋር የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪን ለማልማት የሚውል የ28 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራረመች።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ከዩኒዶ የኢትዮጵያ ተወካይ ካልባሮ አውሬሊያ ፓትሪዚያ ጋር የተፈራረሙ ሲሆን በስነ-ስርዓቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን ሞሀመድም ተገኝተዋል።


 

ፕሮጀክቱ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የጨርቃጨረቅ ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት በኩል የሚተገበር ሲሆን የዘርፉን የሰርኩላር ኢኮኖሚ ለማስተዋወቅና የቴክኖሎጂ ልማትን ለማሳደግ እንደሚውል ተጠቁሟል።

በተጨማሪም ወደ ከባቢ የሚለቀቁ ተረፈ ምርቶችን ለመቀነስና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ ተግባራትንም ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል።

በስምምነቱ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው መንግስት የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም ዩኒዶ በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም