ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የግሉን ባለሃብት ተሳትፎ ለማሳደግ የማበረታቻ ድጋፎች እየተደረጉ ነው- የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ በግብርናው ዘርፍ የግሉን ባለሃብት ተሳትፎ ለማሳደግ መንግስት የፋይናንስና የግብአት ድጋፎች እያደረገ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅነት ከጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የግብርና ግብዓቶች ኤክስፖ ተጠናቋል።


 

በኤክስፖው ማጠቃለያ “በፋይናንስ የተደገፈ ግብርና ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ተካሄዷል።

በፓናል ውይይቱም የግብርና ፋይናንስና ግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎች ያሉ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል። 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ፤ በግብርናው ዘርፍ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ለማሻሻል መንግስት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርናው መስክ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የፋይናንስ አቅርቦትና የግብርና ግብአቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የፋይናንስ ተቋማት በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ባለሀብቶቹ ለግብርና ስራቸው የእርሻ መሳሪያዎች በኪራይና በብድር በመውሰድ እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል። 

የግሉ ዘርፍ በብድርና መሬት አቅርቦት የሚያነሷቸውን ችግሮች ለመፍታት መንግስት በቁርጠኝነት ይሰራል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ባለሀብቶች የሚያገኙትን መሬት በአግባቡ ለልማት ማዋል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የምግብ ዋስትናና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ በሁሉም መስክ ማዘመን እንደሚገባ ጠቅሰው ለዚህም የግሉ ዘርፍ በግብርናው ልማት ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጌታቸው ዋቄ፤ የግብርናውን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ለማበረታታት ባንኩ የወለድ ምጣኔውን ከ11 ነጥብ 5 ከመቶ ወደ 7 ከመቶ ዝቅ ማድረጉን ገልጸዋል። 

የልማት ባንኩ በእርሻ ዘርፍ ለተሰማሩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የእርሻ መሳሪያዎችን በመግዛትና ስልጠና በመስጠት እየደገፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለአርሶ አደሮች የትራክተር ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም በመጥቀስ።

ባንኩ ማዳበሪያና ኬሚካሎችን ጨምሮ ከውጪ የሚገቡ የግብርና ግብአቶችን በአገር ውስጥ መተካት ላይ መስራት ፍላጎት ላላቸው ባለሀብቶች ማበረታቻ ለማድረግ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አንተነህ ደመቀ ኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘርና የደን ውጤቶች፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎችና የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦት እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኮርፖሬሽኑ ለአርሶ አደሮችና ለግሉ ዘርፍ በ2011 ዓ.ም ያቀርብ የነበረውን 214 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር   ወደ 314 ሺህ ኩንታል ከፍ ማድረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የፋይናንስ ተቋማትና በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

በ3ኛው የግብርና ግብዓቶች ኤክስፖ ለተሳተፉ ተቋማት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም