ቀጥታ፡

ኢዜአ አፍሪካን በመረጃ በማስተሳሰር የአህጉሪቷ ድምጽ ለመሆን መስራት ይጠበቅበታል- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አፍሪካን በመረጃ በማስተሳሰር የአህጉሪቷ ድምጽ ለመሆን መስራት እንደሚጠበቅበት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ያስመረቀውን ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጎብኝተዋል፡፡


 

የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎችም አሉት።

በተጨማሪም ለቢሮ አገልግሎት የሚሆኑ በርካታ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ቤተመጽሀፍት፣ የመዝናኛ ማዕከልና ዘመናዊ ጂምናዝየም ያካተተ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ከተመሠረተ 82 ዓመታትን የተሻገረው አንጋፋው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ኢዜአ የኢትዮጵያ ሚዲያ አደረጃጀትና አወቃቀር ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሂደቱም ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ ማስተዋወቁን ገልጸዋል።

በዘመናት ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ አፍሪካን ለማስተሳሰር በርካታ ስራ ማከናወኗንም አንስተዋል። 

ከዚህ አኳያ ኢዜአ በአዲስ ምእራፍ ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች ተደራጅቶ አህጉሪቷን በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ሚና መወጣት በሚችልበት ቁመና ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በቀጣይ አፍሪካን በመረጃ በማስተሳሰር የአህጉሪቷ ድምጽ መሆን እንደሚጠበቅበት ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል በአገር ውስጥ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ትርክት እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና መወጣት እንዳለበት አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ስብራቶች በመጠገን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ በጎ ገጽታን ማስተዋወቅ ላይም በስፋት መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

(ኢዜአ) ብሔራዊ መግባባት የመፍጠርና የሀገር ገፅታ ግንባታ ተልዕኮውን ለማሳካት ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም በመላው ሀገሪቱ 38 ቅርንጫፎችን በመክፈት በቅርቡ የጀመራቸውን ሶማሊኛ እና አፋርኛ ጨምሮ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች አስተማማኝ የዜና ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል።

በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛ እና በፈረንሳይኛ ቋንቋዎችም የኢትዮጵያን ገፅታና እውነታ ለዓለም ተደራሽ እያደረገ ሲሆን፤ አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስም ለተቋሙ ስራ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ይሆናል።

አዲሱ የኢዜአ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በትናንትናው እለት መመረቁ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም