ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ለውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያገለግል ንብረት የሰረቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ለውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያገለግል ንብረት የሰረቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ ፤ጥር 22/2016 (ኢዜአ)፦ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ የዋጋ ግምት ያለው ለውሃ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የሚያገለግል ንብረት የሰረቁ ሰባት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አርባ ዘጠኝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግቢ ውስጥ ነው፡፡
በክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የበሻሌ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደበበ ከለላው እንደተናገሩት ንብረትነቱ የአፍሮፅዮን ኮንስትራክሽን የሆነ እና ለውሃ መስመር ዝርጋታ እንዲውል ታስቦ በመጋዘን ውስጥ ተቀምጦ የነበረው የፕላስቲክ ቧንቧ መገጣጠሚያ ኤልቦ የተሰረቀው ንብረቱን እንዲጠብቁ ሃላፊነት በተሰጣቸው ግለሰቦች ተባባሪነት ነው፡፡
የዋጋ ግምቱ 21 ሚሊዮን 959 ሺህ 6 መቶ ብር የሆነውን ንብረት በለሊቱ ክፍለ ጊዜ ከሰረቁ በኋላ በአጥር በኩል ከግቢው በማውጣት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3- A 55424 አ.አ በሆነ ተሽከርካሪ ለመጫን ሲዘጋጁ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ሶስት ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተጠቅሷል፡፡
ንብረቱን ለመጠበቅ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ተባባሪ የነበሩ ሌሎች አራት ግለሰቦችም በፖሊስ ክትትል ተይዘው የምርመራ ስራው መቀጠሉን ኢንስፔክተር ደበበ መግለጻቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።